ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የጥጥ ምርትን በጥራትና በብዛት በማምረት ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ለማቅረብ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል

ባህር ዳር፤ ነሐሴ 21/2018(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል የጥጥ ልማትን በጥራትና በብዛት በማምረት ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች በግብአትነት ለማቅረብ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

‎በቢሮው የጥጥ ልማት አስተባባሪ አቶ ኤልያስ በላይ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ የሚካሄደው የጥጥ ልማት ከውጭ የሚገባን የጥጥ ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካት የሚያስችል ነው።

‎‎በዚህም በተያዘው የክረምት ወቅት በክልሉ ቆላማ አካባቢዎች 75 ሺህ 717 ሄክታር መሬት በጥጥ መልማቱንና ከዚህም አንድ ሚሊዮን 945 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ ምርት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።


 

በዚህም የጥጥ ምርትን በጥራትና በብዛት በማምረት ለጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪዎች በግብአትነት ለማቅረብ ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

‎ከዘር እስከ ምርት አሰባሰብ ባለው ሂደት ጥራቱን ጠብቆ ጥጥ ለማምረት እየተደረገ ያለውን ጥረት በግብርና ሚኒስቴር ስር የተቋቋመው የጥጥ ልማት ባለስልጣን ክትትልና ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

‎ለአልሚ ባለሃብቶችና አርሶ አደሮች የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በመስጠት የጥጥ ልማት ሥራው በሜካናይዜሽን ታግዞ እንዲከናወን መደረጉንም አመልክተዋል።

‎በጥጥ ልማት ሥራ ከተሰማሩት መካከል በምዕራብ ጎንደር ዞን የምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ አርሶ አደር ዘውዱ ፈቃዴ አምስት ሄክታር መሬታቸውን በጥጥ በማልማት እየተንከባከቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

‎‎ምርታማነታቸውን ለማሳደግና ጥራቱን ለማስጠበቅ የተሰጣቸው ስልጠና ጥራት ያለው ጥጥ በማምረት ለኢንዱስትሪዎች ለማቅረብ እንደሚያግዛቸው አስረድተዋል።

‎መንግስት ለጥጥ ልማት ትኩረት መስጠቱ ሁለት ሄክታር ተኩል ማሳቸውን በጥጥ ለማልማት እንዳነሳሳቸው የገለጹት ደግሞ የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር መከተ ገብሬ ናቸው።

‎በክልሉ ባለፈው የምርት ዘመን በጥጥ ከለማው 58 ሺህ 527 ሄክታር መሬት 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ምርት ለኢንዱስትሪዎች መቅረቡን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያሳያል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም