ቀጥታ፡

የትግራይ ህዝብ በሕገ-ወጡ ሕወሓት የሚደርስበትን ግፍና መከራ ለማስቀረት ቡድኑ ላይ የጀመረውን ትግል ሊያጠናክር ይገባል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 21/2018 (ኢዜአ)፦ በትግራይ ክልል ሕዝብ ላይ ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን የሚያደርሰውን ግፍና መከራ ለማስቀረት ሕዝቡ የጀመረውን ትግል አጠናክሮ በመቀጠል ተጠያቂነት እንዲሰፍን ማድረግ እንደሚያስፈልግ የሥምረት ፓርቲ የምክር ቤት አባልና የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ምክትል ኃላፊ አቶ ጠዓመ ዓረዶም ገለጹ።

አቶ ጠዓመ ዓረዶም በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የሕገ-ወጡ ቡድን አፈሳና አፈና ከጥፋት አጋሩ ሻዕቢያ የተማረው የጥፋትና የጭቆና መንገድ ነው።

በአሁኑ ወቅትም በኢትዮጵያ ከሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ቡድኖች ጋር በመጣመር የሻዕቢያና የግብጽን ተልዕኮ ለማስፈጸም የኢትዮጵያን ሰላምና ደኅንነት ለማናጋት ትንኮሳ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

በተለያዩ የአፋርና አማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የሚፈጽመው ትንኮሳ ሀገርን በማተራመስ የትግራይ ክልልን ሕዝብ ለማጎሳቆል ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

የትግራይ ክልል ሕዝብ እፎይታ የሰጠውን የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በግልጽ በመናድ፣ በምንም ዓላማ ከማይዛመዱ ኃይሎች ጋር ያልተቀደሰ ጋብቻ በመፍጠር ሀገርን ለማተራመስ ሲፎክር እንደሚገኝ ገልጸዋል።

አቶ ጠዓመ በማከልም፤ ሕገ-ወጡ ቡድን በበርካታ ወንጀልና ሰብዓዊ ግፍ የጨቀየ የዘራፊዎች ስብስብ መሆኑን ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅትም በሚፈጽመው ከፍተኛ የዝርፊያና ምዝበራ ተግባር የሀገርን ሃብት እያሸሸ ነው ብለዋል።

በትግራይ ክልል ሕዝብና ወጣቶች ላይ የሚፈጽመው ኢ-ሰብዓዊ እገታ፣ እስር፣ እንግልትና አፈና የሕዝብ ጉስቁልና ምንጭ የሆነ ስግብግብ ቡድን መሆኑን በተግባር እያስመሰከረ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ከግብጽና ሻዕቢያ በሚሰፈርለት የቅጥረኝነት ተልዕኮ ኢትዮጵያን በማተራመስ ከንቱ የህልም ቅዠቱን ለማሳካት እየጣረ መሆኑንም አብራርተዋል።

የትግራይ ክልል ሕዝብና ወጣቶች የሕገ-ወጡን ቡድን የጥፋት ዓላማ አምርሮ በመታገል ሰላም፣ ልማትና አብሮነትን እንደሚሹ በይፋዊ ተቃውሟቸው ድምጻቸውን እያሰሙ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ለዚህም እናቶች፣ ወጣቶች እንዲሁም በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች በቤተ-እምነቶችና በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አማራጮች የቡድኑን እኩይ ሴራ እየኮነኑ መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ ጠዓመ እንዳሉት፣ ሕገ-ወጡ ቡድን ከሕዝብ የተነጠለ የወንጀለኞች ስብስብ ነው። መንግሥት የትግራይን ሕዝብ ጦርነት ከሚያደርስበት ጉስቁልና ለመታደግ የሰጠው ከፍተኛ ትዕግስት የሚደነቅ ነው ብለዋል።

በቀጣይም በሕገ-ወጡ ቡድን በትግራይ ክልል ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን ግፍና መከራ ለማስቀረት የሕግ የበላይነትን በማስከበር ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል።

የሕገ-ወጡ ሕወሓት ቡድን ጠባብ ስብስብ የትግራይ ክልል ሕዝብ ከኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ልማትና ሰላም ተቋዳሽ እንዳይሆን አበክሮ የሚሰራ ጸረ-ሕዝብ መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህም ፓርቲያቸው በትግራይ ክልል ሕዝብ ጫንቃ ላይ የተጫነውን ሕገ-ወጥ ስብስብ ለማስወገድ የጥፋት ቡድኑን የሴራ አጀንዳ የማጋለጥና የመበጣጠስ ሥራ እየሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል።

የትግራይ ክልል ሕዝብና ወጣቶች በቡድኑ ላይ የጀመሩትን ተቃውሞ በማቀጣጠል የጥፋት ቡድኑን ሕልም ማክሸፍ እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም