ቀጥታ፡

የፀጥታ መዋቅሩ ከህዝቡ ጋር ተቀናጅቶ በመስራቱ የውስጥ ባንዳዎች እና የውጭ ባዳዎችን ሴራ አክሽፏል - ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 21/2018 (ኢዜአ)፦ የፀጥታ መዋቅሩ ከህዝቡ ጋር ተቀናጅቶ በመስራቱ የውስጥ ባንዳዎች እና የውጭ ባዳዎችን ሴራ ማክሸፍ መቻሉን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሚሽነሮችና የሰላምና ፀጥታ ኃላፊዎች ሀገራዊ የጋራ የፀጥታ መድረክ እየተካሄደ ነው።

ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የፀጥታ መዋቅሩ ከህዝቡ ጋር በጋራ ተቀናጅቶ በመስራቱ ሰላምን የሚያጸኑ ውጤቶች ተገኝተዋል።

ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ በሰላም እንዲከናወን፣ በየደረጃው ያለው የፖሊስ ሰራዊት፣ የፀጥታና አስተዳደር ኃላፊዎች፣ ሚሊሻዎች፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት በጋራ በማቀድ መስራታቸውን አመልክተው፤ በዚህም በሀገርም ሆነ በዓለም በአርአያነት የሚጠቀስ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ መካሄድ መቻሉን ተናግረዋል።

ሁል ጊዜ ኢትዮጵያ በችግር እንድትቆይ ሰላሟን ለማናጋት የሚሹ የውስጥ እና የውጭ ጠላቶች በመገናኘት በርካታ ሴራዎችን እንደሚያቅዱ ያወሱት ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ፤ እነዚያን ሴራዎች በየደረጃው ህይወታቸውን ጭምር በመክፈል እና ሴራውን በማምከን፣ የሀገርን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ ዛሬ ለተደረሰበት ደረጃ መሰራቱን ተናግረዋል።

መድረኩ በቀጣይም የኢትዮጵያ ጠላቶች ሰላምና ደህንነት ለማናጋት ከውስጥ ባንዳዎች እና ከውጭ ባዳዎች ጋር ተገናኝተው የሚሰሩትን ሴራ ሁሉ ለማክሸፍ፣ ሰራዊቱ አሁንም ዝግጁ መሆኑን የሚያረጋግጥበት እና ለቀጣይ ተልዕኮዎች ራሱን የሚያዘጋጅበት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የቱሪስቶች መዳረሻ ከመሆን ባለፈ ትላልቅ የአህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ኹነቶች የሚካሄድባት ተመራጭ ሀገር መሆኗን አንስተዋል።

የእነዚህ ኹነቶች በሰላም እና ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከናወኑ የፖሊስ ሰራዊቱ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በጋራ ከፍተኛ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን አክለዋል።

በቀጣይም ለሚካሄዱ ትላልቅ ሀገራዊ ኹነቶች በጋራ መወያየት፣ በጋራ ማቀድ እና በመዘጋጀት የጠላትን ሴራ እያከሸፍን በሰላም እንዲካሄዱ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የዛሬው መድረክም ​በዋናነት የተከናወኑትን ሥራዎች እና በእዚያ ውስጥ የተገኙ ጥሩ ተሞክሮዎች እና ያጋጠሙን ክፍተቶች በመለየት በቀጣይ ደግሞ ለሚኖር ተልዕኮ ከወዲሁ ለመዘጋጀት ያለመ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ጠላቶችን ሴራ በማክሸፍና የሀገሪቱን ብልጽግና እውን ለማድረግ የሚከናወኑ ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ የጋራ ስራችንን ልናጠናክር ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም