ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የከፍታ ጉዞ ማሳያ የአፍሪካውያን ኩራት - የኢትዮጵያ አየር መንገድ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከንግድ ተቋምነት ባለፈ የአፍሪካውያንን አንድነት፣ የነፃነት ታሪክና የጋራ ብልጽግና ስትራቴጂን በሰማይ ላይ የገነባ እውነተኛ የፓን አፍሪካዊነት ተምሳሌት ነው።

አህጉሪቱ ገና ከቅኝ አገዛዝ ቀንበር ባልተላቀቀችበትና የእርስ በእርስ ትስስር በሌለበት እ.አ.አ ከ1945 ጀምሮ የአፍሪካን ሕዝቦችና መሪዎች በማገናኘት የታሪክ ህያው ምስክር ሆኖ አገልግሏል።ይህ አየር መንገድ፣ የአፍሪካ አዲስ መንፈስ የሚለውን መፈክሩን በተግባር ያረጋገጠ ብሔራዊና አህጉራዊ ኩራትም ነው።

አየር መንገዱ ለአፍሪካዊያን የጋራ ዕድገት የሚሠራ መሆኑን የሚያረጋግጠው ዋነኛው ተግባሩ፣ የገንዘብና የቴክኒክ አቅም አንሷቸው የፈረሱ ወይም የተቸገሩ የሌሎች አፍሪካ ሀገራትን ብሔራዊ አየር መንገዶች በጋራ ባለቤትነት መልሶ የማቋቋምና የማጠናከር ዘላቂ ስትራቴጂው ነው።

በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ትርፋማና ግዙፍ ተቋም ከመሆን ባለፈ የአህጉሪቱን የአቪዬሽን ዘርፍ በጋራ ለማሳደግ የአፍሪካ አየር መንገዶችን የማቋቋምና የመደገፍ” ስትራቴጂካዊ ሥራዎችን በስፋት እያከናወነ ይገኛል።

ተቋሙ ከአፍሪካ አየር መንገዶች ማህበር (AFRAA) እና ከተለያዩ  የአፍሪካ ሀገራት መንግስታት ጋር በመተባበር በአህጉሪቱ ዘርፈ ብዙ ስኬቶችን አስመዝግቧል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የባለቤትነት ድርሻ በመያዝ እና የማኔጅመንት (የአመራር) አገልግሎት በመስጠት በርካታ አየር መንገዶችን በማቋቋምና በማጠናከር ቀዳሚውን ሚና እየተጫወተም ይገኛል።

በዚህም በምዕራብ አፍሪካ ቶጎ ላይ መቀመጫውን ያደረገው አስካይ (ASKY) አየር መንገድ፣ የማላዊ አየር መንገድ፣ የዛምቢያ አየር መንገድ እና የኮንጎ አየር መንገድ የጊኒ አየር መንገድ እና ሌሎችም የአቪዬሽን ኢንቨስትመንቶች ላይ በሚያደርገው ተሳትፎ ጠንካራ ክንድነቱን አስመስክሯል።

አየር መንገዱ አብዛኛውን የኩባንያዎቹን የባለቤትነት ድርሻና ትርፍ ለባለቤት ሀገራቱ መንግሥታት በመተው፣ የአመራር፣ የስልጠናና የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ የአፍሪካ አቪዬሽን በጋራ እንዲያድግ አድርጓል።

በአቪዬሽን እሴት ሰንሰለት (Aviation Value Chain) ውስጥ ያለውን መዋቅራዊ የበላይነት በመጠቀምም ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት አየር መንገዶች የተቀናጀ የቴክኒክና የስልጠና ድጋፍ ይሰጣል።

ተቋሙ በእነዚህ አየር መንገዶች ውስጥ ስትራቴጂካዊ የባለቤትነት ድርሻ በመያዝ፣ አብዛኛውን የኩባንያዎቹን የባለቤትነት መብትና የንግድ ትርፍ ለባለቤት ሀገራቱ መንግሥታት በመተው፣ ሙሉ የኦፕሬሽንና የማኔጅመንት ኃላፊነቱን በመውሰድ አፍሪካውያን ራሳቸውን እንዲችሉ አድርጓል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ አየር መንገዶችን የማቋቋምና የማጠናከር ስራ ሙሉ በሙሉ በፓን አፍሪካዊነት እና በእውነተኛ አፍሪካዊ የትብብር መንፈስ ላይ የተመሠረተ ታላቅ አህጉራዊ ስራ ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚከተለው ሁለገብ ስትራቴጂ ግቡ የገበያ የበላይነትን መቆጣጠር ሳይሆን፣ አቪዬሽን ለሌላቸው ወይም አየር መንገዶቻቸው ለፈረሱባቸው አፍሪካውያን ወንድም ሀገራት የቴክኒክና የአመራር አቅምን ማካፈልም ነው።

የአፍሪካ አየር መንገዶችን በጋራ ባለቤትነት ሲያቋቁም የኢኮኖሚ ጥቅሙን ብቻ አስልቶ ሳይሆን፣ በአፍሪካ የነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት መሠረት የአህጉሪቱን የሰዎችና የዕቃዎች ዝውውርን በማቀላጠፍ የጋራ አፍሪካዊ ብልጽግናን ለማምጣት በማለም ነው።

ይህ አካሄድ አህጉሪቱ ከውጭ አየር መንገዶች ጥገኝነት እንድትላቀቅ የሚያደርግ እውነተኛ የፓን አፍሪካዊነት መግለጫ ነው።

የራሱን የአብራሪዎች ኢንጂነሮች እና የበረራ አስተናጋጆችን የሚያሰለጥንበትን ዘመናዊ የአቪዬሽን አካዳሚ በመገንባትም ለአቪዬሽን ዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ ቁልፍ ሚናውን እየተጫወተም ይገኛል።

የስልጠና እና የጥገና አቅሙ ከፍተኛ እንደመሆኑም ለተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት የአቪዬሽን ባለሙያዎች ፣ እንዲሁም ከአህጉሪቱ ውጭ ላሉ አየር መንገዶች የስልጠና ፣የጥገና እና የቴክኒክ አገልግሎት በመስጠት የአህጉሪቱ የአቪዬሽን የጀርባ አጥንት መሆኑን አስመስክሯል።

ይህ አህጉራዊ ትስስር ሀገራት የየራሳቸውን የአቪዬሽን ዘርፍ እንዲያጠናክሩና በንግድ፣ በቱሪዝም እና በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ የአፍሪካ ህብረት የአጀንዳ 2063 ራዕይ እንዲሳካ የበኩሉን ሚና ይጫወታል።

በየዓመቱ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን የሚያገኘው አየር መንገዱ እንደ ኤይር ባስ ኤ 350-1000 ያሉ ዘመኑን የዋጁ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን በመግዛት በአፍሪካ የመጀመሪያ በመሆን በብቸኝነት የሚያበር ሲሆን በአፍሪካ ትልቁን የአውሮፕላን ጥገና ማዕከል እና ዘመናዊ የካርጎ (የጭነት) ተቋም በመገንባትም አገልግሎቱን አዘምኗል::

በመላው ዓለም 26 የሚሆኑ ታላላቅ አየር መንገዶች ያሉበት የስታር አሊያንስ አባል በመሆን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ግዙፉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየዓመቱ ለሀገራችን የሚያስገኘው ገቢም ከዋነኛዎቹ የኢኮኖሚ አውታሮች ተርታ ቀዳሚው ያደርገዋል።

ዓለምን ያስጨነቀው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተከሰተበትና ታላላቅ ዓየር መንገዶች በኪሳራ ስራ ባቆሙበት ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለው ቁርጠኝነትና ጠንካራ አመራር አማካኝነት በካርጎ/በጭነት አገልግሎት ለአፍሪካዊያንና ሌሎች የዓለም ሃገራት መድሃኒቶችንና የህክምና መገልገያዎችን ጨምሮ የተለያዩ ጭነቶችን በማጓጓዝ አለኝታነቱንም ትርፋማነቱንም አረጋግጧል።

ለአፍሪካውያን የሚሰራ እውነተኛ አፍሪካዊ ተቋም መሆኑን በተግባር ያረጋገጠው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ዛሬም እንደ ትላንቱ የአህጉሪቱ የልማትና የአንድነት ድልድይ ሆኖ ቀጥሏል።

አየር መንገዱ አሁንም የአፍሪካ አዲስ መንፈስ ሆኖ አህጉሪቱን ወደ ላቀ የብልጽግና እና የጋራ የከፍታ ምህዋር መምራቱን በጽናት ይቀጥላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም