በዞኑ በማህበራዊ ድጋፍ አገልግሎት የተሰባሰቡ የትምህርት ቁሳቁሶች ለተማሪዎች እየተሰራጩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ በማህበራዊ ድጋፍ አገልግሎት የተሰባሰቡ የትምህርት ቁሳቁሶች ለተማሪዎች እየተሰራጩ ነው
ደብረ ብርሃን፤ ነሐሴ 20/2018 (ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በክረምት የማህበራዊ ድጋፍ አገልግሎት የተሰባሰቡ 75 ሺህ ደርዘን ደብተርና ሌሎች የትምህርት ቁሶች እየተሰራጩ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።
በዞኑ “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ“ በሚል መሪ ሀሳብ በበጎ ፈቃደኞች የተሰባሰቡ የትምህርት ቁሳቁስ ወላጆቻቸው አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች እየተሰራጨ ነው።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መካሻ ዓለማየሁ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፣ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የማህበረሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር በማቃለል በኩል ጉልህ አስተዋጾ እያደረገ ነው።
በተያዘው ክረምትም በዞኑ 985 ሺህ 759 በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በማሳተፍ ትምህርት፣ ግብርናና ጤናን ጨምሮ በ17 የሥራ ዘርፎች የማህበራዊ መደጋገፍን የሚያጎለብቱ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የመንግስት ሠራተኞች ከመደበኛ ሥራቸው በተጨማሪ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሳተፍ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ውጤታማ በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስገንዝበዋል።
የዞኑ ትምህርት መምሪያ ምክትል ሀላፊ አቶ ዋሲሁን ብርሃኑ በበኩላቸው እንዳሉት በዞኑ በ2019 የትምህርት ዘመን 612 ሺህ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር የምዝገባ ሥራ ተጀምሯል።
ተማሪዎች በትምህርት ቁሳቁስ እጦት ምክንያት ከትምህርት ገበታ እንዳይቀሩ በማህበራዊ ድጋፍ አገልግሎት 75 ሺህ ደርዘን ደብተርና ሌሎች የትምህርት ቁሶችን በማሰባሰብ የማሰራጨት ሥራ መጀመሩንም ገልጸዋል።
በዛሬው ዕለትም ለ1 ሺህ 255 ተማሪዎች ለእያንዳንዳቸው አንድ ደርዘን ደብተር እና 12 እስክርቢቶ በድጋፍ መሰጠቱን ነው የተናገሩት።
የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፉ ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ተማሪዎችን ቁጥር በመቀነስ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑም አመልክተዋል።
የደብተርና የእስክርቢቶ ድጋፍ ካገኙ ተማሪዎች መካከል ተማሪ ወንጌላዊት ይልማ የተደረገላት ድጋፍ ለቤተሰቦቿ እፎይታን የሚሰጥ መሆኑን ተናግራለች።
ሌላው ተማሪ ኪሩቤል ንጋቱ በበኩሉ የተደረገለት ድጋፍ ለማህበረሰቡ ያለውን ፍቅርና አክብሮት እንደጨመረለት ገልጿል።