ቀጥታ፡

የሪፎርም ስራዎች የአገር ውስጥ የመድኃኒት አቅርቦት እንዲያድግ አስችለዋል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 20/2018 (ኢዜአ)፦ባለፉት ዓመታት የተተገበሩ መሠረታዊ የሪፎርም ሥራዎች የአገር ውስጥ የመድኃኒት አቅርቦት እንዲያድግ ማስቻላቸውን የኢትዮጵያ መድሀኒት አቅራቢ አገልግሎት አስታወቀ።

አገልግሎቱ በ5ኛው የአፍሪካ የአቅርቦት ሰንሰለት የልህቀት ሽልማት (ASCEA 2026) ከፍተኛውን የ«Gold Award» ሽልማት ማሸነፉም ተገልጿል።

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፤ ባለፉት አራት ዓመታት የተተገበሩ መሠረታዊ የሪፎርም ሥራዎችን በትኩረት አከናውኗል።

ከተከናወኑት ዋና ዋና ተግባራት መካከል አቅርቦትን ወደ ዲጂታል ሥርዓት ማሸጋገር፣ የግዥ ሥርዓቱን ማዘመንና ግልጽ ማድረግ፣ የክምችትና ሥርጭት አሠራርን ማስተካከል እንዲሁም የምርቶች አቅርቦት ሰንሰለት ቅንጅትን ማጠናከር ይገኙበታል።

ይህንንም ተከትሎ በርካታ ውጤቶች የተመዘገቡ ሲሆን ሪፎርሙ የሀገር ውስጥ የመድኃኒት አቅርቦት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያድግ ማስቻሉንም አመልክተዋል።

በተለይም ቴክኖሎጂን በመጠቀም አጠቃላይ የግዥና የክምችት ሥርዓቱን በኤሌክትሮኒክ መንገድ ማዘመን መቻሉ የአገልግሎት ቅልጥፍናን እንደጨመረው ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

ከዚህ ቀደም ረጅም ጊዜ ይወስድ የነበሩ አሠራሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ መቻሉን አስታውቀው ይህም የደንበኞችን እርካታ በከፍተኛ ሁኔታ ከማሳደጉ ባሻገር አሠራሩን ወጪ ቆጣቢ ማድረጉንም ገልጸዋል።

ይህም በአገልግሎቱ የተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት አህጉራዊ እውቅናም እያስገኘለት መሆኑን ጠቁመዋል።

የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያዎች አቅርቦት ሰንሰለት የዘረጋው ቀልጣፋና ዘመናዊ ዲጂታል አሠራር አህጉራዊ ዕውቅና ያገኘ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በዚሁ መሠረት  በ5ኛው የአፍሪካ የአቅርቦት ሰንሰለት የልህቀት ሽልማት (ASCEA 2026) ከፍተኛውን የ«Gold Award» ሽልማት ማሸነፍ መቻሉንም አስታውቀዋል።

ይህ ሽልማት አገልግሎቱ የሕክምና አቅርቦት ሰንሰለቱን ሙሉ በሙሉ በዲጂታል ለማስደገፍና ተደራሽነቱን ለማስፋት የሠራቸው ስኬታማ ሥራዎች ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ እውቅና ወደፊት አገልግሎቱን አህጉራዊ ተወዳዳሪና ይበልጥ ቀልጣፋ ለማድረግ ለተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች ትልቅ ብርታት እንደሚሆን አክለዋል።

 

 


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም