ኢትዮጵያ የጤና ሥርዓቱን በፋይናንስ በመደገፍ የዘርፉን የሰው ኃይል አቅም በመጠንና በጥራት እያሳደገች ትገኛለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የጤና ሥርዓቱን በፋይናንስ በመደገፍ የዘርፉን የሰው ኃይል አቅም በመጠንና በጥራት እያሳደገች ትገኛለች
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 20/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የጤና ሥርዓቱን በፋይናንስ በመደገፍ የዘርፉን የሰው ኃይል አቅም በመጠንና በጥራት እያሳደገች መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ ገለጹ።
በአፍሪካ ጠንካራና ቀጣይነት ያለው ብቁ የጤና ባለሙያዎችን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ከአባል ሀገራት ጋር በትብብር ትሰራለችም ብለዋል።
76ኛው የዓለም የጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ኮሚቴ ጉባኤ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መካሄዱን ቀጥሏል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ብቁና ሥነ ምግባር የተላበሰ የጤና ባለሙያ ማፍራት የሚያስችል ስትራቴጂ ገቢራዊ አድርጋለች።
ኢትዮጵያ የጤና ሰራተኞች ስትራቴጂ ገቢራዊ በማድረግ የጤናውን ዘርፍ የሰው ኃይል አቅም ከ50 በመቶ በላይ ማሳደግ ችላለች ብለዋል።
በዚህም በገጠርና ምቹ ባልሆኑ አካባቢዎች ላሉ የጤና ሰራተኞች ምቹ የሥራ ከባቢን በመፍጠርና ድጋፍ በማድረግ እንዲበረታቱ መደረጉን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2026 እስከ 2035 የሚተገበረውን የአፍሪካ የጤና ሰራተኞች ስትራቴጂ በመደገፍ ለተግባራዊነቱ ከአባል ሀገራቱ ጋር በትብብር ትሰራለች ብለዋል።
በአፍሪካ ጠንካራና ቀጣይነት ያለው የጤና ሰራተኞች ግንባታ ዕውን እንዲሆን ከሕብረቱ አባል ሀገራት ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግረዋል።
በዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና የጤና ሥርዓትና አገልግሎት ክላስተር ዳይሬክተር ዶክተር አደልሄድ ኦንያነጎ በበኩላቸው፤ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአፍሪካ የጤና ሰራተኞች ላይ የጎላ አሉታዊ ተፅዕኖ ቢያሳድርም እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ከ2017 በኋላ መሰረታዊ ለውጥ ተመዝግቧል ብለዋል።
በአሕጉሪቱ ቀጣይና የጤና ዘርፍ ስትራቴጂዎችን፣ ፖሊሲዎችንና ዓለም አቀፍ የጤና ስትራቴጂዎችን ገቢራዊ በማድረግ የአፍሪካን የጤና ሰራተኛ በ2013 ከነበት 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በ2024 ወደ 5 ነጥብ 7 ሚሊዮን ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።
ይሁን እንጂ አፍሪካ በባለሙያዎች ፍልሰት፣ በአካላዊ ጫናና ከሥራ በማቋረጥ ሳቢያ በጤናው ዘርፍ ላይ አደጋ እንዲደቀንበት ማድረጉ አልቀረም ብለዋል።
በመሆኑም የጤና ሥርዓቱን ጠንካራና ዘላቂነት ያለው ለማድረግ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ከ2026 እስከ 2035 የሚቆይ የአፍሪካ የጤና ሰራተኞች አጀንዳ ገቢራዊ መደረጉን ገልጸዋል።
በዚህም እስከ 2035 ጠንካራ የጤና ተቋማትን ከመገንባት ባለፈ አሕጉሪቱ ቢያንስ ከ3 ሚሊዮን ያላነሰ ተጨማሪ የጤና ሰራተኛ ያስፈልጓታል ብለዋል።
ይህን ግብ ለማሳካት ጠንካራ የአስተዳደር ሥርዓት መገንባት፣ የስልጠና ማዕከላት ማስፋፋት፣ የተጠያቂነትን ሥርዓት ማስፈን እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።