ቀጥታ፡

የመዲናዋን የአረንጓዴ ትራንስፖርት ራዕይ እውን ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 20/2018 (ኢዜአ)፦የመዲናዋን የአረንጓዴ ትራንስፖርት ራዕይ እውን ለማድረግ የተከናወኑ ዘመናዊ የትራንስፖርት መሰረተ ልማቶች ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገባቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የከተማዋን ፈጣን እድገት የሚመጥን ዘመናዊ የትራንስፖርት መሰረተ ልማት ግንባታ እውን ለማድረግ በተከናወኑ የተቀናጁ ተግባራት ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውንም ጠቁመዋል።

ከንቲባዋ ይህንን የተናገሩት የተገነቡ የተቀናጁ የትራንስፖርት ተርሚናሎች፣ የመኪና ማቆሚያዎችና የንግድ ማዕከላት ምረቃ መርሃ ግብር ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ነው። 


 

ከተማ አስተዳደሩ ኅብረተሰቡ አገልግሎቶችን በፍጥነትና በጥራት የሚያገኝባቸውን በርካታ ዘመናዊ መሠረተ ልማቶች ግንባታ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት አብቅቷል ብለዋል።

ዛሬው ለምረቃ የበቁት የታክሲና የአውቶቡስ አገልግሎት ትራንስፖርት የሚሰጡ መሰረተ ልማቶች ህብረተሰቡ በተረጋጋ ሁኔታ ዐረፍ ብሎ አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችሉ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

ከተማዋ የጀመረችውን የአረንጓዴ ትራንስፖርት ራዕይ እውን ለማድረግ በትራንስፖርት መሰረተ ልማት ግንባታዎቹ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ሀይል መሙያዎች መካተታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የከተማዋን የትራፊክ ፍሰት ማቃለል የሚያስችሉ ሰፋፊ የመኪና ማቆሚያዎች ከነሙሉ አገልግሎታቸው ተዘጋጅተው ለሕዝብ ጥቅም ክፍት ተደርገዋል ነው ያሉት፡፡

ከተማ አስተዳደሩ የህብረተሰቡን የትራንስፖርት አገልግሎት ፍላጎት ከመመለስ ባሻገር የአካባቢ ጥበቃን ያማከሉ አረንጓዴ የትራንስፖርት አማራጮችን እያሰፋ እንደሚገኝም ከንቲባ አዳነች ገልጸዋል፡፡

በዚህም በመዲናዋ አረንጓዴ ትራንስፖርትን ለመገንባት በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

እነዚህ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ መሰረተ ልማቶች ከተማዋ ወደ አረንጓዴ ትራንስፖርት የምታደርገውን ሽግግር ያፋጥናሉ ብለዋል፡፡


 

በአሁኑ ወቅት የህዝብ ትራንስፖርትንና የግል ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ የመኪና ማቆሚያ አቅም ከ180 ሺህ በላይ መድረሱን ከንቲባዋ ጨምረው አስታውቀዋል፡፡

በእነዚህ የትራንስፖርትና የመኪና ማቆሚያ መሰረተ ልማቶች ግንባታና አገልግሎት አሰጣጥ ብቻ እስከ አሁን ከ20 ሺህ በላይ ለሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዲዛይንና ግንባታ ሥራዎች ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር አያልነሽ ሐብተማሪያም በበኩላቸው፤ ቢሮው ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ፍጥነትና ጥራት ተጠናቅቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ብርቱ ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡

መሰረተ ልማቶቹ የትራፊክ ፍሰቱን የሚያቀላጥፉና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ሀይል መሙያዎችን ያካተተ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በውስጣቸው የንግድ ሱቆች፣ ካፌና ሬስቶራንቶች፣ አሳንሰሮችና የቲኬት መቆረጫ ቢሮዎች እንደተገነባላቸውም ገልጸዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም