በሰሜን ጎንደር ዞን 29 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ሰብል ለምቷል - ኢዜአ አማርኛ
በሰሜን ጎንደር ዞን 29 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ሰብል ለምቷል
ጎንደር ፤ነሐሴ 20 /2018 (ኢዜአ)፡- በሰሜን ጎንደር ዞን በያዝነው ክረምት 29 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆን መሬትን በስንዴ ሰብል መሸፈን መቻሉን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ፋሲካ መርሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የስንዴ ልማቱን በማስፋት ለኢንዱስትሪዎች ግብዓትና ለገበያ የሚተርፍ ምርት ለማምረት እየተቻለ ነው፡
በ2018/19 የመኸር ምርት ዘመንም 35 ሺህ 290 ሄክታር መሬት በስንዴ ሰብል በማልማት ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።
እስካሁን በተደረገ ጥረትም 29 ሺህ 439 ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን የአረምና የተባይ መከላከል ተግባር እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
አርሶ አደሩ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ እንዲሁም ምርጥ ዘር በአግባቡ እንዲጠቀም በማድረግ፣ ምርታማነቱን በሄክታር በአማካይ 31 ኩንታል ለማድረስ እየተሠራ መሆኑንም አስረድተዋል።
በተጨማሪም በመካናይዜሽን በመታገዝ በኩታ ገጠምና በመስመር አሠራር በመዝራት የታቀደውን ምርት ለመሰብሰብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
የዘር ሥራው አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመው፤ ይህም የታቀደውን መሬት ሙሉ በሙሉ ለማልማት የሚያስችል መሆኑን አስገንዝበዋል።
በዞኑ በተያዘው የመኸር ምርት ዘመን በአጠቃላይ ከ156 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት እየተሠራ እንደሚገኝ ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።