ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር አሰናበቱ - ኢዜአ አማርኛ
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር አሰናበቱ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 20/2018 (ኢዜአ)፦የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ጃንግ ካንግን አሰናብተዋል።
በብሔራዊ ቤተ መንግሥት በተከናወነው የስንብት መርሃ ግብር ላይ በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ጃንግ ካንግ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያ ወዳጅነት በጠንካራ ታሪካዊ መሠረት ላይ የተገነባ ነው።
የሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት በስትራቴጂክ ጉዳዮች ላይ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
በተለይም በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ በሚደረጉ ጉብኝቶች፣በኢኮኖሚ ትብብርና በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ዘርፎች አበረታች እድገት መመዝገቡን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በቆዩባቸው ዓመታትም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የበኩላቸውን ገንቢ ሚና መወጣታቸውን አምባሳደሩ ገልጸዋል።
በቀጣይም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ መጠን ማሳደግ የደቡብ ኮሪያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያላቸውን ኢንቨስትመንትና የኢኮኖሚ ተሳትፎ ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በተጨማሪም በሕዝቦች መካከል ያለውን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትና የባህል ልውውጥ የበለጠ ማጎልበት እንደሚገባ አምባሳደሩ ገልጸዋል።
የሁለቱ ሀገራት ታሪካዊና ጠንካራ ወዳጅነት በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸው፣ በኢትዮጵያ ላሳለፉት መልካም ጊዜ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።