ቀጥታ፡

ፕሬዝዳንቱ የገለጹት የኢትዮጵያ እውነት

ከሐምሌ 8 ጀምሮ በአዲስ አበባ ኮንቬንሽን ማዕከል ሲካሔድ የቆየው የሃገራዊ ምክክር ጉባኤ ማጠቃለያ በስኬት ማለቁ ተበስሯል።

የውጭና የሃገራት እንግዶች የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የሃገር ሽማግሌዎች አባገዳዎች የኃይማኖት አባቶች ኮሚሽነሮችና ተመካካሪዎች በታደሙበት በዚህ መድረክ ላይ ፕሬዝዳንቱ ያሰሙት ድምጽ ጆሮ ገብ ነበር። የሁሉንም ትኩረት የሳበ።

ለመሆኑ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በማጠቃለያ መድረኩ ላይ ምን ብለው ነበር? በዚህ ንግግራቸውስ ምን መልዕክት አስተላለፉ?

የሀገራዊ ምክክሩ በስኬት መጠናቀቅ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ታሪክ የማይታወቀውና ያልተለመደው የሆነበት ነው ይህ ምከክር ልዩነቶችን ከምክክር ይልቅ በኃይል ለመፍታት የመሞከር አባዜም ወደ ታሪክነት መሸጋገሪያው ነው

ፕሬዝዳንቱ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ተረክ /political discourse/ ውስጥ በዘፈቀደ ሲገለጹ የሚሰሙትኢትዮጵያ መስቀለኛ መንገድ ላይ ነችኢትዮጵያ ልትበተን ነውኢትዮጵያ ልትፈርስነው የሚሉና መሰል አገላለጾች የፖለቲከኞች እንጀራ መብያ እንጂ የኢትዮጵያ መንገድ መገለጫ እንዳልሆነ ያነሳሉ።

ይልቁንም ኢትዮጵያን የማይገልጹና ከፍላጎታችን፣ ከሀገራዊ መሻቶቻችን ጋር አብረው የማይሄዱት እነዚህ አገላለጾች መነሻቸው ዝንታለም በሌሎች ሀሳብና ርዕይ የሚነግዱ የሀሳብ ተከታዮች እንጂ ኢትዮጵያውያን ፈጽሞ የሚናገሩት ቃል አይደለም ይላሉ።

ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ጉዞ የሚሆነው መስቀለኛ ሳይሆን ቀጥ ያለ፣ ርቱዕ የእድገትና የህብረት መንገድ ብቻ መሆኑንም አስምረውበታል።

ምክክር ማህበራዊ ባህላችን ውስጥ ያለንና የቆየ ሀብታችን ቢሆንም ይሄንን ነባር ባህል የፈተናዎቻችን መድህን የሀገር ግንባታችን ካስማ እንዲሆን መልክና ቅርጽ ተበጅቶለት ይፈጸም ዘንድ ቢያንስ በርሳቸው እድ እንደማያስታውሱ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ የዚህን ሂደት ታሪካዊ ዋጋና ሀገራዊ ፋይዳ በማሰላሰል ለሀሳቡ እውንነት ለተጉት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(/) ምስጋና አቅርበዋል።

የሀገራዊ ምክክሩ ውጥንና ዓላማ ኢትዮጵያን ማዕከል በማድረግ ዘመንን ሊያሻግሩና ሀገርን ሊያጸኑ በሚችሉ የሀሳብ አውዶች ዙሪያ መወያየት እንደመሆኑም በመድረኩ የታየው ይሄው ነበር።

በፕሬዝዳንት ታዬ የተገለጹት አምስቱ የሃገራዊ ምክክር ፋይዳዎች፦

በፕሬዝዳንት ታዬ የተገለጹት አምስቱ የሃገራዊ ምክክር ፋይዳዎችም መነሻቸው ይሄንኑ ታሳቢ ያደረጉ ናቸው የጋራ መሻትን ማጎልበት ቀዳሚው ሲሆን ልዩነቶችን በመሻገር የጋራ እጣፈንታንና ራዕይን የሚያጸና እውቀት የተንሸራሸረበት መድረክ መፍጠሩ ነው።

ሁለተኛው ደግሞ ምክክሩ ኢትዮጵያውያንን ወደ ስክነትና እርጋታ እንዲሸጋገሩ ያስቻለ፣ የፖለቲካ ውይይቱም ከስሜታዊነት ወጥቶ በሰከነ አስተዋይ በሆነ መንገድ እንዲመራም ያስቻለ መሆኑን ነው።

ፕሬዝዳንቱ በሦስተኛነት የጠቀሱት የምክክሩ ትልቁ ፋይዳ ደግሞ የይቅርታ እና የስርየት ጎዳና እንዲፈጠር መሰረት መጣሉ ሲሆን ከደመኝነት እና ከተቃርኖ ፖለቲካ በመውጣት በይቅርታና በመተሳሰብ የጋራ ጉዞን ለመቀጠል ምቹ ሁኔታን መፍጠሩ ነው።

የተለመደው የፖለቲካ ማጠንጠኛ ከሆነው ከአምባጓሮና ከነፍጥ በዘላቂነት በመላቀቅ የፖለቲካ ልምምዳችን በሰላምና በመደማመጥ ላይ እንዲመሰረት ሃገራዊ ምክክሩ በር መክፈቱ በአራተኛነት ያነሱት ነጥብ ነው

ሌላኛው በአምስተኛነት የጠቀሱት የምክክሩ ማህበራዊ ፋይዳም በመከባበርና በሰመረ ቋንቋ፣ ከኃይለ ቃል በፀዳ መልኩ ለመወያየት የሚያስችል አቅም እንዳለን ያሳየንም ነው።

እንደ ሀገር ፈተና ባጋጠመን ጊዜ አንዳንድ ወዳጅ ሀገራት ከናንተ የተማርነው በህብረት ቆማችሁ ቀኝ ገዢዎችን ማንበርከክ ሆኖ ሳለ ለምን የውስጥ ጉዳያችሁን ለመፍታት ወደ ነፍጥ ታደላላችሁ? የሚል የወዳጅ ጥያቄ አዘውትሮ እንደሚቀርብም አንስተዋል።

መንግስት የነበረ አካል ወደ ሽፍትነት የተለወጠበትን አጋጣሚ ጨምሮ ኢትዮጵያውያን ውጥንቅጥ ችግር ሲያጋጥማቸው መቼውንም ቢሆን መውጫ መንገድ አጥተው እንደማያውቁም ጠቅሰዋል።

ለዚህም ህልውናችንን የሚፈታተኑ ጉዳዮች ሲያጋጥሙን ሀገር እየጠበቅንም፣ እየመከርንም ኢትዮጵያችንን ማፅናት መቻላችን ነው ብለዋል።

የዚህ መሰረቱ ደግሞ ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ስልጣኔ፣ እውቀትና እውነትን አጋምዳ የያዘች በመሆኗ ችግር ሲያጋጥመን በጋራ ቆመን ጠላትን የምንመክተው የዳበረ፣ የጥንት ሀገር ስልጣኔ ባለቤት በመሆናችን ነው ይላሉ።

እንደኛ የፖለቲካ እይታ ቢሆን ሌላ ድርሳን ነበረ። አጋምዶ የያዘን ግን አንዱ ጥንታዊ ሀገር ባለቤቶች በመሆናችን ነው። ሀገር ደግሞ የጋራ ላብ፣ የጋራ ደም፣ ተከሻና ጉልበት ውጤት ናት ሲሉም ገልጸዋል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት የውስጥ ችግር ባጋጠመን ወቅት፣ በአለም አቀፍ መድረክ እጅግ የማይመቹ ቃላት በኢትዮጵያ ላይ ተነጣጥረው እንደነበረ አንስተው የጋራችንን ሳይሆን የተወሰኑ የክፋት መንገድን የመረጡ ኃይሎችን ብቻ በመመልከት የኢትዮጵያ ማህበራዊ ትስስር ተበጥሷል፣ ወደነበረበት ለመመለስም ኢትዮጵያውያን ተስኗቸዋል በማለት ለማስተከዝ የሞከሩ እንደነበሩም አስታወሰዋል።

አንዳንዶቹማ በዚህ ሀገራዊ የሀሳብ ጉባኤ ወቅት ሳይቀር የእንመካከር እንወያይ ሀሳብ ለሀሳብ እንለዋወጥ የሚለውን ጥሪ እንደ ትልቅ አጋጣሚ ከመውሰድ ይልቅ፣ ለክፋት መጠንስሻና ግጭት ማውጠንጠኛ ሊያደርጉ ሲባዝኑ መታዘባቸውን አንስተዋል።

እነዚህን የመሰሉ ግለሰቦችና ቡድኖች የሺህ ዓመታት ጥብቅ ማህበራዊ ሸማችንን በቅጡ ያልተረዱ፣ የህዝባችንን የውስጥ ጥንካሬ ያላወቁ ናቸው ይሏቸዋል ፕሬዝዳንቱ።

እኛ ኢትዮጵያውያን የተራሮች፣ የሸለቆዎች፣ የደጋዎች፣ የወንዞች ልጆች ነን። የኢትዮጵያ ህዝብ ወንዞቹን ለመሻገርና ለመግራት የሚያስፈልገውን ትዕግስት ጠንቅቆ የሚያውቅ ህዝብ ነው።

በእርግጥም አባይን የሚያቋርጥ ብቻ ሳይሆን ታሪክን የሚያሻግር ሁሉ ከነፋስና ወጀብ የበረታ ታላቅ የትዕግስት መከተሪያ ሊኖረው እንደሚገባ ያወቀ ብልህ ህዝብም ነው። ትዕግስት ስንቁ ነው። የሚሻገረውም በትዕግስተኛነትና በብርታት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም