የመድሀኒትና ህክምና መሣሪያዎች አቅርቦት አገልግሎት ዲጂታል ሪፎርም እውቅና አገኘ - ኢዜአ አማርኛ
የመድሀኒትና ህክምና መሣሪያዎች አቅርቦት አገልግሎት ዲጂታል ሪፎርም እውቅና አገኘ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 20/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ መድሀኒት አቅራቢ አገልግሎት ለሀገሪቱ የመድሀኒትና የሕክምና መገልገያዎች አቅርቦት ሰንሰለት የዘረጋው ቀልጣፋና ዘመናዊ ዲጂታል አሠራር አህጉራዊ እውቅና ማግኘቱን የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ ገለጹ።
አገልግሎቱ በ5ኛው የአፍሪካ የአቅርቦት ሰንሰለት የልህቀት ሽልማት (ASCEA 2026) ከፍተኛውን የ«Gold Award» ሽልማት ማሸነፉም ተገልጿል።
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፤ ባለፉት አራት ዓመታት በተተገበሩ መሠረታዊ የሪፎርም ሥራዎች በትኩረት አከናውኗል።
ከተከናወኑት ዋና ዋና ተግባራት መካከል አቅርቦትን ወደ ዲጂታል ሥርዓት ማሸጋገር፣ የግዥ ሥርዓቱን ማዘመንና ግልጽ ማድረግ፣ የክምችትና ሥርጭት አሠራርን ማስተካከል እንዲሁም የምርቶች አቅርቦት ሰንሰለት ቅንጅትን ማጠናከር ይገኙበታል።
ይህንንም ተከትሎ በርካታ ውጤቶች የተመዘገቡ ሲሆን ሪፎርሙ የአገር ውስጥ የመድኃኒት አቅርቦት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያድግ ማስቻሉንም አመልክተዋል።
በተለይም ቴክኖሎጂን በመጠቀም አጠቃላይ የግዥና የክምችት ሥርዓቱን በኤሌክትሮኒክ መንገድ ማዘመን መቻሉ የአገልግሎት ቅልጥፍናን እንደጨመረው ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
ከዚህ ቀደም ረጅም ጊዜ ይወስድ የነበሩ አሠራሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ መቻሉን አስታውቀው ይህም የደንበኞችን እርካታ በከፍተኛ ሁኔታ ከማሳደጉ ባሻገር አሠራሩን ወጪ ቆጣቢ ማድረጉንም ገልጸዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ይህ በአገልግሎቱ የተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት አህጉራዊ እውቅናም እያስገኘለት መሆኑን ጠቁመዋል።
የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያዎች አቅርቦት ሰንሰለት የዘረጋው ቀልጣፋና ዘመናዊ ዲጂታል አሠራር አህጉራዊ ዕውቅና ያገኘ ሲሆን በቅርቡም በ5ኛው የአፍሪካ የአቅርቦት ሰንሰለት የልህቀት ሽልማት (ASCEA 2026) ከፍተኛውን የ«Gold Award» ሽልማት ማሸነፍ መቻሉንም አስታውቀዋል።
ይህ ሽልማት አገልግሎቱ የሕክምና አቅርቦት ሰንሰለቱን ሙሉ በሙሉ በዲጂታል ለማስደገፍና ተደራሽነቱን ለማስፋት የሠራቸው ስኬታማ ሥራዎች ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ እውቅና ወደፊት አገልግሎቱን አህጉራዊ ተወዳዳሪና ይበልጥ ቀልጣፋ ለማድረግ ለተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች ትልቅ ብርታት እንደሚሆን አክለዋል።