ቀጥታ፡

የመደመር መንግሥት የአገልግሎት አሰጣጥን ለማቀላጠፍ ቴክኖሎጂን እንደ ቁልፍ መሣሪያ በመጠቀም እመርታዊ ለውጦችን እያመጣ ይገኛል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 20/2018 (ኢዜአ)፦የመደመር መንግሥት የሕዝብ አገልግሎት አሰጣጥን ለማቀላጠፍ ቴክኖሎጂን እንደ ቁልፍ መሣሪያ በመጠቀም እመርታዊ ለውጦችን እያመጣ መሆኑን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መሶብ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዮናስ አለማየሁ ገለጹ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጭነት የተጀመረው የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣የዜጎችን እንግልት በመቀነስና የመንግሥት አሰራርን በማዘመን ረገድ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ይገኛል።

ማዕከሉ በቴክኖሎጂ የታገዘ ቀልጣፋ አሰራርን በአንድ ቦታ ላይ በማቅረብ፣ዜጎች የሚፈልጓቸውን አገልግሎቶች በአንድ ቦታ ፈጣን፣ጥራት ያለውና ምቹ በሆነ ሁኔታ እንዲያገኙ አድርጓል።

ይህም የመንግሥትን አገልግሎት አሰጣጥ ከማሳለጡ ባለፈ፣ አጠቃላይ አሰራሩን ግልጽ በማድረግ ብልሹ አሰራርን በከፍተኛ ሁኔታ መከላከል ችሏል፡፡

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መሶብ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዮናስ አለማየሁ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የመንግሥት የአገልግሎት አሰጣጥ በሂደት መቀየርና መሻሻል የሚገባው ትልቅ ክፍተት በመሆኑ መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት መቋቋሙን ገልጸዋል።

አገልግሎቶቹን ዲጂታላይዝድ ከማድረግ ባሻገር ተበታትነው የሚገኙ የመንግሥት አገልግሎቶችን ወደ አንድ ማዕከል በማምጣት የተሳለጠ እና ውጤታማ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

ማዕከሉ የተበታተኑ የመንግሥት አገልግሎቶችን አቀናጅቶ ለዜጎች በአንድ ማዕከል መስጠት ሲሆን ይህም ስኬታማ ነበር ብለዋል።

አገልግሎቶቹን በማቀናጀት ብቻ ሳይወሰን ለዜጎች የሚሰጠው አገልግሎት እርካታን የሚያመጣ እንዲሆን ማድረግ ሌላው የማዕከሉ ዋና ዓላማ መሆኑን ጠቅሰው፥ በዚህ ረገድም ውጤታማ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት በአገር አቀፍ ደረጃ ከ110 በላይ ማዕከላት መድረሱንና እስካሁን ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ተገልጋዮች አገልግሎት መሰጠቱን ጠቅሰዋል።

የዜጎችን የአገልግሎት ፍላጎት በፍጥነትና በቅልጥፍና ለማሟላት የተለያዩ የአገልግሎት ሞዳሊቲዎችን ተግባራዊ እያደረገ እንዳለም ገልጸዋል።

በአካል ወደ ማዕከሉ መምጣት የማይችሉ ዜጎችን ተደራሽ ለማድረግ የሞባይልና የተንቀሳቃሽ አገልግሎት መጀመሩን ጠቁመዋል።

በዚህም በፌደራል ደረጃ ሁለት እና በአዲስ አበባ ከተማ አንድ በድምሩ ሦስት ተንቀሳቃሽ የመሶብ አገልግሎቶች ሥራ መጀመራቸውን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪ የኦንላይን አገልግሎትና የአፕሊኬሽን ሞዳሊቲዎችን በመጠቀም አገልግሎቶችን እያቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም