ቀጥታ፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች የገጠሩ ክፍል የአኗኗር ዘይቤ እንዲዘምን እያስቻሉ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 20/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች እና የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እየጎለበቱ መምጣታቸው የገጠሩ የሀገራችን ክፍል የአኗኗር ዘይቤ እንዲዘምን እያስቻሉ መሆኑን የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር መኩሪያ ሀይሌ (ዶ/ር) ገለጹ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ተጠሪ የሆኑት የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በጋራ በመሆን በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ባሌ ዞን ጊኒር ወረዳ ሸወዴ ቀበሌ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተለያዩ ተግባራትን በይፋ አስጀምረዋል።


 

የተቋማቱ አመራሮች እና ሰራተኞች በምስራቅ ባሌ ዞን የሚገኘውን አስደናቂውን የሶፍ ዑመር ዋሻም ጎብኝተዋል፡፡ 

ተቋማቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወነ የሚገኘውን የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሀ ግብር ለመደገፍ ዓላማ አንግበው መነሳታቸው ተጠቁሟል። 

የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር መኩሪያ ሀይሌ (ዶ/ር) እንደገለጹት በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እና የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እየጎለበቱ መምጣታቸው የገጠሩ የሀገሪቱ ክፍል የአኗኗር ዘይቤ እንዲዘምን እያስቻሉ ነው። 

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ልምድ እየዳበረ መምጣቱ የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራትን ማጠናከሩንም  አብራርተዋል።

በከተማም ሆነ በገጠር የሚከናወኑ የኮሪደር ልማት ስራዎችን ለዚህ በአበይት ማሳያነት ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ ሁሉም በየተሰማራበት መስክ ህዝቡንና ሀገሩን በቀናነት ማገልግል እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።

ከኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ጋር በመተባበር በዘንድሮ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ባሌ ዞን ጊኒር ወረዳ ሸወዴ ቀበሌ የሚከናወኑ አጠቃላይ ከ100 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ ልዩ ልዩ የበጎ ፈቃድ ተግባራትን ማከናወን ጀምረናል ብለዋል።

ከበጎ ፈቃድ ተግባራት መካከል ከሀገራዊው የገጠር ኮሪደር ልማት ስራ ጋር በተቀናጀ መልኩ 20 መኖሪያ ቤቶችና አንድ መዋለ ሕፃናት እንዲገነቡ የመሠረተ ድንጋይ መቀመጡን ጠቅሰው፤ ከሚገነቡት መኖሪያ ቤቶች መካከል አምስቱ ቤቶች በምስራቅ ባሌ ዞን አስተዳደር እንደሚገነቡም ገልጸዋል።


 

540 ለሚሆኑ ተማሪዎች ለመማር ማስተማር የሚያገለግሉ የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉንና የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር መከናወኑንም አክለዋል።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አይድሩስ ሀሰን በበኩላቸው፤ በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜጎችን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ የበጎ ፈቃድ ተግባራት ላይ ኮሚሽኑ እየተሳተፈ ይገኛል ብለዋል።

ሁለንተናዊ ልማቷ የተረጋገጠባት ኢትዮጵያን ለትውልዱ ለማሻገር የበጎ ፈቃድ ተግባራት ወሳኝ መሆናቸውንም ጨምረው ተናግረዋል።


 

በመሆኑም ከፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የበጎ ፈቃድ ተግባራትን በምስራቅ ባሌ ዞን ማከናወን ጀምረናል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና የምታደርገውን ግስጋሴ ለማፋጠን የክረምት የበጎ ፈቃድ ተግባራትን በተጠናከረ መልኩ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።


 

የምስራቅ ባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ጃርሶ ቦሩ በዞኑ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የቤት እድሳት፣ የትምህርት ተቋማት ግንባታ፣ ደም ልገሳ እና የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብርና ሌሎች ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።     

በተቋማቱ የተጀመሩ የበጎ ፈቃድ ተግባራት ነዋሪዎች የተለያዩ አገልግሎቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ ለማድረግ በርካታ ፋይዳዎች እንዳሉትም ጨምረው ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም