ሀገራዊ ምክክሩ በሀገር ጉዳይ በጋራ በመምከር ዘላቂ ሰላም እና ጠንካራ ሀገር መገንባት እንደምንችል በተግባር ያየንበት ነው- የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ በሀገር ጉዳይ በጋራ በመምከር ዘላቂ ሰላም እና ጠንካራ ሀገር መገንባት እንደምንችል በተግባር ያየንበት ነው- የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች
አምቦ ፤ ነሐሴ 20/2018 (ኢዜአ)፡-ሀገራዊ ምክክሩ በሀገር ጉዳይ በጋራ በመምከር ዘላቂ ሰላም እና ጠንካራ ሀገር መገንባት እንደምንችል በተግባር ያየንበት ነው ሲሉ የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
በኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ የቆዩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትና ሁለንተናዊ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር አሳታፊ የሆነ ሀገራዊ የምክክር ሂደት ተካሂዶ በስኬት መጠናቀቅ ችሏል።
በተለይም የሀገራዊ ምክክር ጉባዔው በኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የነበረውን ችግሮችን በኃይል የመፍታት የፖለቲካ ባህል በመቀየር፣ ልዩነቶችን በንግግርና በውይይት ብቻ መፍታት እንደሚቻል በተግባር ያሳየ ታሪካዊ ሁነት ሆኗል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች፤ ሀገራዊ ምክክሩ የዚህ ትውልድ ጉልህ አሻራ ያረፈበትና ለቀጣዩ ትውልድ የምትመች ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ጠንካራ መሰረት ያኖርንበት ነው ብለዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ በሀገር ጉዳይ በጋራ በመምከር ዘላቂ ሰላም እና ጠንካራ ሀገር መገንባት እንደምንችል በተግባር ያየንበት ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አቶ ደለሳ ሚዴክሳ፤ የምክክር ጉባኤው ለዘመናት የዘለቁ አለመግባባቶችን በኃይል ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀራርበን ለመፍትሄው የተመከረበት ታሪካዊ ሁነት መሆኑን አንስተዋል።
ለዘመናት የተሻገሩ የፖለቲካና ማህበራዊ ስብራቶችን በምክክር በመፍታት ለሁላችንም የምትመች ሀገር ለመገንባት መሰረት ያኖርንበት ታሪካዊ ክስተት ነው ብለዋል።
ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ወይዘሮ ቶለሺ ፈይሳ እና አቶ ደበላ ጌታሁን፤ ኢትዮጵያዊያን ከጫፍ ጫፍ ተሰባስበው በሀገራቸው ጉዳይ የመከሩበት ሀገራዊ የምክክር ሂደት አስደሳች መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ተቀራርበው በመምከር የጋራ መፍትሄ የተለሙበት፣ ዘላቂ ሰላም እና ጠንካራ ሀገር መገንባት እንደምንችል በተግባር ያየንበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ለአርባ ስድስት ቀናት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የመከረው የምክክር ጉባኤ በስኬት የተጠናቀቀ መሆኑም ይታወቃል።