የሀገራዊ ምክክሩ ስኬት ኢትዮጵያን ወደ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ ያሸጋግራል -የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የሀገራዊ ምክክሩ ስኬት ኢትዮጵያን ወደ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ ያሸጋግራል -የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች
ቦንጋ፣ነሐሴ 20/2018 (ኢዜአ)፡-የሀገራዊ ምክክሩ በስኬት መጠናቀቅ ችግሮችን በጋራ በመፍታት ኢትዮጵያን ወደ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ ለማሸጋገር ምቹ መደላድል እንደሚፈጥር የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ከሀምሌ 8 ጀምሮ በተለዩ ስምንት አጀንዳዎች ላይ ሲያካሂድ የቆየውን ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በስኬት ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው፡፡
በጉዳዩ ለይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች የምክክሩ በስኬት መጠናቀቅ ችግሮችን በጋራ ፈትቶ ኢትዮጵያን ወደ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ ለማሸጋገር ምቹ መደላድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
ከከተማው ነዋሪዎች መካከል ወጣት ትዕግስቱ ጴጥሮስ እንዳለው ላለመግባባትና ለግጭት መንስኤ የሆኑ የቆዩ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት የተጀመረው ሂደት ሃገርን ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው፡፡
ሂደቱ እኔ አውቅልሀለው በሚል ፍላጎትን በሃይል ለማስፈጸም ሲደረግ የነበረን አካሄድ በመቀየር ዜጎች በሀገራቸው ላይ በጋራ መክረው በአንድነትና ተግባብተው ለመኖር ያላቸውን ፍላጎት ያሳዩበት ነው ብሏል፡፡
ሀገራዊ ምክክር ችግሮችን በውይይትና በምክክር የመፍታት ባህልን ከማዳበር ባለፈ በብዙ መልኩ የሀገራችንን መፃኢ ዕድል ያሳምረዋል ሲልም ገልጿል።
ሌላኛው የከተማው ነዋሪ አቶ ጥላሁን ደሳለኝ በበኩላቸው ሐገራዊ የምክክር ጉባኤው ዜጎች ልዩነት በፈጠሩና ሳያግባቡ በቆዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተው የጋራ ምክረሀሳብ ያስቀመጡበት ምቹ ምህዳር መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ከዚህ ቀደም ንግግር ተደርጎባቸው የማያውቁ ሃገራዊና ህገመንግስታዊ ጉዳዮች ላይ ጭምር ውጤታማ ውይይት በማድረግ ኢትዮጵያን ወደ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ የሚያሸጋግር ተግባር መከናወኑን ገልጸዋል፡፡
ሀገራዊ ምክክሩ እርስ በእርስ የመነጋገርና የመደማመጥ ባህልን በማዳበር ለሀገር ዘላቂ ሰላምና አንድነት ትልቅ መሰረት መጣሉን የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ ነቢላ አህመድ ናቸው።
ከዚህ ቀደም ላለመግባባት መንስኤ በሆኑ ጉዳዮች ለይ ቁጭ ብለን ባለመነጋገራችን እንደሀገር ብዙ ዋጋ ከፍለናል ያሉት አስተያየት ሰጪዋ ሀገራዊ ምክክሩ ታሪካዊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ወጣት አለማየሁ ወልደሚካል የተባለ ነዋሪ በበኩሉ ምክክሩ በስኬት መጠናቀቁ ችግሮቻችንን በውስጥ አቅም በመፍታት ለጠንካራ ሀገር መንግስት ግንባታ ትልቅ መሠረት ይጥላል ብሏል፡፡
ሀገራዊ ምክክሩ በሀገራችን ውይይት ባህል ሆኖ እንዲቀጥል መሰረት መጣሉንና ይህን ለማስቀጠል ከታች ጀምሮ ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ አመልክቷል።
ሀገራዊ ምክክሩ ተቀራርቦ መነጋገር፣ መከባበርና መደማመጥ ካለ የማይፈቱ የሚመስሉ ችግሮችን በመፍታት ሀገርን በጋራ ማስቀጠል እና ዕድገቷን ማፋጠን እንደሚቻል ትልቅ ማሳያ ነው ሲልም ገልጿል።