ሀገራዊ ምክክሩ የሁሉንም ወገን ድምፅ ያዳመጠና የኢትዮጵያ አሸናፊነት የተረጋገጠበት ታሪካዊ መድረክ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ የሁሉንም ወገን ድምፅ ያዳመጠና የኢትዮጵያ አሸናፊነት የተረጋገጠበት ታሪካዊ መድረክ ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 20/2018 (ኢዜአ)፦የተካሄደው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የሁሉንም ወገን ድምፅ ያዳመጠ እና የኢትዮጵያ አሸናፊነት የተረጋገጠበት ታሪካዊ መድረክ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች ገለጹ።
ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ለአርባ ስድስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በስኬት ተጠናቋል።
በጉባኤው ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የዘለቁ የአለመግባባት ስብራቶችን በሐሳብ የበላይነትና በጥበብ መፍትሔ መስጠት እንደሚችሉ በተግባር አሳይቷል፡፡
ኢዜአ ያነጋገራቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ ለአርባ ስድስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ አሳታፊና አካታች መሆኑን ገልጸዋል።
የምክክር ጉባኤው ከአራቱም የሀገሪቱ ማዕዘናት የተውጣጡ አራት ሺህ ተመካካሪዎች በመሳተፍ ለኢትዮጵያ የሚበጁ ምክረ ሐሳቦችን ማዋጣት የቻሉበት መሆኑን ተናግረዋል።
ከነዋሪዎች መካከል መልካም በንቲ እንደገለጸችው፤ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሕዝቡ እኩል እንዲመክርና እንዲወከል በማድረጉ ከፍተኛ ሀገራዊ ስሜትን የሚያነቃቃና ባለቤትነትን የሚያረጋግጥ መሆኑን አስታውቀዋል።
በታሪካችን ውስጥ የነበሩ የታሪክ ስብራቶችን ለማቃናት፣ ቅሬታዎችን ለመፍታትና የቆዩ ችግሮችን ለማስተካከል ሂደቱ ወሳኝ እንደነበረም አመልክታለች፡፡
ጉባኤው ኢትዮጵያን ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ለማሻገርና ኢትዮጵያን በጽኑ መሠረት ላይ ለማስቀጥል ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ገልፃለች።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ሱራፌል ዳርጌ በበኩላቸው፤ ሀገራዊ ምክክሩ በኢትዮጵያ የቆዩ ችግሮችን በራሳችን አቅምና በጋራ ውይይት ለመፍታት የሚያስችል ታሪካዊና ከፍተኛ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
ጉባኤው ዘላቂ ሰላሟ የተጠበቀና በጽኑ መሠረት ላይ የተገነባች ሀገርን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ወሳኝ ድርሻ እንዳለው ጠቁመዋል።
በተለይም በሕዝቦች መካከል ያለውን ወንድማማችነትና የጋራ እሴቶችን በማጠናከር ረገድ ወደ ተሻለ አንድነት የሚያመጣ መንገድ መሆኑን አመልክተዋል።
የተካሄደው ሀገራዊ ምክክር የሁሉንም ወገን ድምፅ በማደመጥ የኢትዮጵያ አሸናፊነትና የበላይነት የተረጋገጠበት ታሪካዊ መድረክ መሆኑን የገለጸው ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ወጣት አላዛር ረዘነ ነው።
ጠንካራና የጸና ሀገራዊ አንድነት እንዲፈጠር ሲንከባለሉ የቆዩ መሠረታዊ ችግሮችን በጥቅል የመፍታትና ለጥያቄዎችም ዘላቂ ምላሽ የመስጠት በኩል መድረኩ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።
በተለይም ችግሮችን በተበታተነና በተነጠለ መንገድ ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ፣ በጋራ በመቆምና በአንድነት በመካከር ለችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት ምቹ ሁኔታንና አዲስ ተስፋን የፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ ችግሮችን በራስ አቅም የመፍታት ከፍተኛ ዕድል የፈጠረ መሆኑን የገለፀው ደግሞ ሌላኛው የመዲናዋ ነዋሪ ወጣት እዮብ ተኬ ነው።
ሀገራዊ ምክክሩ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያስቀጥሉና የሚያጠናክሩ ወሳኝ ምክረ ሐሳቦች የተንሸራሸሩበት መድረክ መሆኑን አስታውቋል።
በመሆኑም በምክክሩ የመጡ መልካም አጋጣሚዎችንና ውጤቶችን ለማጽናት እንዲሁም ወደ ተግባር ለመቀየር ሁላችንም የበኩላችንን ድርሻ ልንወጣ ይገባል ሲል ጥሪ አቅርቧል።