ቀጥታ፡

ለአዲስ አበባ ተጨባጭ እድገት በቅንነትና በታማኝነት መስራታችንን እንቀጥላለን- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 20/2018 (ኢዜአ)፦ ለአዲስ አበባ ከተማ ተጨባጭ እድገት በቅንነት እንዲሁም በታማኝነት መስራታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ የመዲናዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባዋ የዘመነ መሰረተ ልማት፤ የዘመነ አገልግሎት ለዘመናዊ ከተማ! በሚል ባስተላለፉት መልዕክት፤ በከተማዋ አራት ዘመናዊ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች፣ ተርሚናሎችና ገበያ ማዕከላት (በጎተራ፥ ቦሌ፣ የካ እና ቀበና) ዛሬ መርቀው አገልግሎት ማስጀመራቸውን ጠቁመዋል።

እነዚህ መሰረተ ልማቶች የትራፊክ መጨናነቅን የሚያቃልሉ፣ የትራንስፖርት ሥርዓትን የሚያሻሽሉ፣ ህዝባችንን ከዝናብና ፀሐይ እንግልት የሚከላከሉ፣ በርካታ የስራ እድሎችን የሚፈጥሩ ምቹ ፣ ንፁህ እና የሰውን ክብር የሚመጥኑ የዘመነ አገልግሎት የሚሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

መሰረተ ልማቶቹ በአንድ ጊዜ በርካታ ተሽከርካሪዎችን የማስተናገድ ዓቅም ያላቸው ዘመናዊ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች፣ የታክሲ እና የአውቶቡስ ተርሚናሎች፣ የአየር ብክለትን የሚከላከሉ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጅ ማድረጊያዎች፣ ሰፊ የህዝብ መዝናኛ ስፍራዎች፣ የንግድ ሱቆች፣ ካፍቴሪያና ሬስቶራንቶች እና የልጆች መጫወቻና ማረፊያ ስፍራዎች የተሟሉላቸው ናቸው።

በተጨማሪም ምቹ የተሳፋሪ መጠበቂያ ስፍራዎች፣ የአስተዳደር እና የትኬት መቁረጫ ቴክኖሎጂዎች፣ አሳንሰሮች እና ንፁህ መፀዳጃ ቤቶች እንዲሁም የደህንነትና የአደጋ ቅድመ መከላከል ሥርዓቶች የተሟሉላቸው ሆነው የኢኮኖሚና የማህበራዊ አገልግሎትን ለማሳለጥ ትልቅ አስተዋጽዖ የሚያበረክቱ እንደሆኑም ከንቲባዋ ተናግረዋል።

ከለውጡ በፊት ሶስት ሺህ ብቻ የነበረውን የአንድ ጊዜ የተሽከርካሪ ማቆሚያ አቅም እና ምንም ያልነበረንን ተርሚናል በአሁኑ ጊዜ በጥራትና በፍጥነት የተገነቡ፣ ዘመናዊ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎችን እና ተርሚናሎችን ከ170 ሺህ በላይ ማድረስ መቻሉን አመልክተዋል።

ለከተማችን ነዋሪዎች ተጠቃሚነት በተጨባጭ ቃላችንን በተግባር ስራዎችን እየፈጸምን በቅንነትና በታማኝነት እየሰራን እንገኛለን። አዲስ አበባ ከዚህ በላይ ይገባታል ቀጣይም ከሰራነው በላይ እንተጋለን! ብለዋል።

ከንቲባዋ የዛሬዎቹ ፕሮጀክቶች እውን እንዲሆኑ ለተጉ፣ ላስተባበሩ የዲዛይንና ግንባታ ስራዎች ቢሮ አመራሮችና ሰራተኞች፣ የትራንስፖርት ቢሮ አመራሮች፣ ኮንትራክተሮች፣ አማካሪዎች በዚህ ስራ ለተሳተፉ በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም