ቀጥታ፡

በሀዋሳ የሐይቅ ዳርቻ እና የኮሪደር ልማት ሥራዎችን በተያዘው ጊዜ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ነው-ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ

ሀዋሳ፣ ነሐሴ20/2018 (ኢዜአ)፡-በሀዋሳ ከተማ የተጀመሩ የሐይቅ ዳርቻ እና የኮሪደር ልማት ሥራዎችን በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ፡፡

ሀዋሳ ከተማን ሳቢ፣ ምቹና ይበልጥ ተመራጭ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች በርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ እና በሌሎች የሥራ ሃላፊዎች ተጎብኝቷል። 


 

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት ከተማዋ ያላት የተፈጥሮ ውበት ይበልጥ ጎልቶ እንዲወጣ የኮሪደር ልማት ሥራው ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

በአሁኑ ወቅት ግንባታው እየተካሄደ ያለው የሐይቅ ዳርቻ እና የኮሪደር ልማት ሥራዎች ከተማዋን ይበልጥ ለኑሮ፣ ለኢንቨስትመንት፣ ለመዝናኛነት እና ለኮንፈረንስ ምቹና ተመራጭ እንደሚያደርጋት ጠቁመዋል።


 

እነዚህ የልማት ሥራዎች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ የክልሉ መንግስት መላውን ህዝብ በማስተባበር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።


 

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው በከተማዋ ለአራተኛ ዙር እየከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ሥራ ከጥቃቅን ሥራዎች በስተቀር ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

የሀዋሳ ሐይቅ ዳርቻ ልማት ሥራም በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ በቀን ለ24 ሰዓታት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

ለሐይቅ ዳርቻ ልማቱ ህዝቡን በማስተባበር እስካሁን ድረስ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መቻሉንም ተናግረዋል።

በልማት ሥራዎች ጉብኝት ላይ የሲዳማ ክልልና የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም