የእንጦጦ ፓርክ የጎብኝዎችን ቀልብ የሚስብ ማራኪ የቱሪዝም መዳረሻ ነው -ዓለም አቀፍ ጎብኝዎች - ኢዜአ አማርኛ
የእንጦጦ ፓርክ የጎብኝዎችን ቀልብ የሚስብ ማራኪ የቱሪዝም መዳረሻ ነው -ዓለም አቀፍ ጎብኝዎች
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 20/2018 (ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ በተራራ ሰገነት ላይ የተከተመው የእንጦጦ ፓርክ የጎብኝዎችን ቀልብ የሚስብ ማራኪ የቱሪዝም መዳረሻ መሆኑን ዓለም አቀፍ ጎብኝዎች ገለጹ።
ፓርኩ ከተመረቀ ማግስት ጀምሮ የሀገር ውስጥና የዓለም አቀፍ ጎብኚዎች የስበት ማዕከል መሆን እንደቻለ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሕዝብ መዝናኛ ቦታዎችና ፓርኮች ኮርፖሬሽን አስታውቋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት አዲስ አበባን የውበት አክሊል ካቀዳጇት ማራኪ የገበታ ለሸገር እመርታዊ የመስህብ መዳረሻ ፕሮጀክቶች ግምባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው።
በገበታ ለሸገር ፕሮጀክት የተገነቡት የአንድነት፣ የወዳጅነትና የእንጦጦ ፓርኮችም አዲስ አበባን ማራኪ የከተሜነት ውበት በማጎናጸፍ ለቱሪስት መዳረሻነት ምቹ ምኅዳርን ፈጥረዋል።
በአዲስ አበባ የእንጦጦ ፓርክን የጎበኙ ዓለም አቀፍ ቱሪስቶች ለኢዜአ እንዳሉትም፤ አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የከተሜነት ምኅዳርን መጎናጸፍ ያስቻሏትን የልማት ስኬቶች አስመዝግባለች።
በገበታ ለሸገር በተራራ ሰገነት ላይ የተገነባው የእንጦጦ ፓርክም ተፈጥሯዊ አቀማመጥን ከተስማሚ የአየር ሁኔታ ጋር አሰናስሎ የተገነባ ማራኪ የቱሪስት መዳረሻ ማዕከል መሆኑን ገልጸዋል።
ከዓለም አቀፍ ጎብኝዎች መካከል የመናዊው ኃይል ሁሴን፤ እንጦጦ ፓርክ ተፈጥሮን ከምቹ የአየር ሁኔታ ጋር አሰናስሎ የያዘ የመዳረሻ ስፍራ መሆኑን ተናግረዋል።
በተራራ ሰገነት ላይ የተገነባው የእንጦጦ ፓርክ የተጎናጸፈው ገጽታም የአዲስ አበባን ዕይታ፣ የአረንጓዴ መናፈሻና ንጹህ የአየር ሁኔታ ከስሜት የሚጋባ ልዩ ስፍራ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያውያን የእንግዳ ተቀባይነት ባህልና አክብሮት፣ የምግብ ዝግጅትና የቡና ሥርዓትም የጎብኝዎችን የቆይታ ጊዜ በማራዘም ልዩ ትዝታን የሚያጎናጽፍ ድንቅ እሴት መሆኑን ገልጸዋል።
በቆይታቸው ያገኙትን ደስታም ቀጣይ ጓደኞቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውን በመያዝ የኢትዮጵያን ድንቅ የመዳረሻ ስፍራዎች ለመጎብኘት ዕቅድ እንዳላቸው አረጋግጠዋል።
ሌላኛዋ ዓለም አቀፍ ጎብኝ ታይላንዳዊቷ ኦንጂራ ራቺንዳ በበኩላቸው፤ አዲስ አበባ የአፍሪካ ሁለንተናዊ የከተሜነት ለውጥ መገለጫ ከተማ ሆናለች ብለዋል።
የእንጦጦ ፓርክም ለሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ጎብኝዎች ልዩ የመንፈስ እርካታን የሚያጎናጽፍ ማራኪ የመስህብ መዳረሻ ሥፍራ መሆኑን ገልጸዋል።
ዓለም አቀፍ ጎብኝዎችም የኢትዮጵያ ማራኪ የተፈጥሮ፣ ሰው ሰራሽ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች የሚገበኙበት ዕድል መኖሩን መልዕክት አስተላልፈዋል።
ጅቡቲያዊው ዑመር አሕመድ በበኩላቸው፤ የእንጦጦ ፓርክ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ፣ ውበት፣ ንጹህ አየርና ማራኪ የከተማ ዕይታ ማራኪ የመዳረሻ ስፍራ እንዳሰኙት ገልጸዋል።
ፓርኩ በርካታ ውብ የመዝናኛና የመንቀሳቀሻ ስፍራዎች አሉት፤ ከእንጦጦ ፓርክ ላይ ሆኖ የአዲስ አበባን ሙሉ ገጽታ መመልከትም መንፈስን ያድሳል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሕዝብ መዝናኛ ቦታዎችና ፓርኮች ኮርፖሬሽን የክትትል ሥራ አስፈጻሚና የእንጦጦ ፓርክ ኃላፊ መዝገቡ ይስማው፤ የእንጦጦ ፓርክ በ2013 መስከረም ወር ክፍት ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ ከ5 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች የስበት ማዕከል ሆኗል ብለዋል።
የፓርኩም ቀደም ሲል በከፍተኛ አንግልት በእንጨት ለቀማ ይተዳደሩ የነበሩ እናቶችን ጨምሮ በርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ዕድል እንደፈጠረ ገልጸዋል።