ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ሽግግርን ውጤታማ በማድረግ በኩል ለአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት የሆነ ተግባር አከናውናለች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 20/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በግብርና ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እያከናወነች ባለችው ተግባራት ለአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት መሆኗን የአህጉር አቀፍ ተቋማት የስራ ሀላፊዎች እና ባለሙያዎች ገለጹ።

በአፍሪካ ህብረት ልማት ኤጀንሲ የግብርና እና የገጠር ትራንስፎርሜሽን ዋና ፕሮግራም ባለሙያ ክሌመንት አድጆርሎሎ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የአፍሪካ ሀገራት የምግብ ስርዓታቸውን ለማጠናከርና ፍላጎታቸውን በራስ አቅም ለማሟላት በትብብር ሊሰሩ ይገባል።

በአህጉሪቱ እያደገ የመጣውን የህዝብ ፍላጎት በራስ አቅም ለማሟላትና ጠንካራ የምግብ ስርዓትን ለመገንባት ከኢትዮጵያ ተሞክሮ መውሰድ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የግብርና ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ የንግድ ስርዓትንና አጠቃላይ የግብርና ዘርፍ የእሴት ሰንሰለቱን ማጠናከር እንደሚገባም ገልፀዋል።

በምግብ ራስን ለመቻልና ምርታማነትን ለማሳደግ የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ብሎም በለውጥ ሂደት ላይ ተሳታፊ የሚያደርጉ ስራዎች ወሳኝ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በዘርፉ ያከናወነቻቸውን ተግባራት እና ያስመዘገበቻቸውን ውጤቶች ሌሎች ሀገራት ሊጋሩት እንደሚገቡም አክለዋል።

ኢትዮጵያ ስንዴን በስፋት በማምረት የሀገር ውስጥ ፍጆታ ከማሟላት በተጨማሪ ለውጭ ገበያ ማቅረብ መጀመሯ የሀገር ውስጥ የግብርና ምርትን ማሳደግ ያለውን አስተዋፅኦ ያመላክታል ብለዋል።

ኢትዮጵያን በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የግብርና እና የምግብ ስርዓትን ከአካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም የሚያስችል ተግባርን በማስተሳሰር የሚደረግ ውጤታማ ተግባር ማሳያ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግና ለአህጉር አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኝ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በአጀንዳ 2063 የቀጣናዊ ስትራቴጂክ ትንተናና እውቀት ድጋፍ ሰጪ ስርዓት ዲፓርትመንት ኃላፊ ፖል ጉቲጋ የኢትዮጵያ የግብርና ሽግግር ለቀጣናው ሀገራት ትምህርት የሚሆን ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ፣የኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማጠናከርና የአርሶ አደሮችን ገቢ ለማሳደግ ያከናወናቸው ውጤታማ ተግባራት የአፍሪካ ሀገራት ሊወስዷቸው የሚገቡ ተሞክሮዎች መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ መንግስት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት አስደናቂ እንደሆኑም ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም