በክልሉ የተጀመሩ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች በአዲሱ በጀት አመትም ይበልጥ ተጠናክረው ይቀጥላሉ- ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የተጀመሩ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች በአዲሱ በጀት አመትም ይበልጥ ተጠናክረው ይቀጥላሉ- ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ
ባህር ዳር፤ ነሐሴ 20/2018 (ኢዜአ)፡-የህዝቡን ጥያቄዎች መሰረት በማድረግ የተጀመሩ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች በአዲሱ በጀት አመትም ይበልጥ ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።
የአማራ ክልል የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 ዕቅድ የትውውቅ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ፈተናዎችን በማለፍና ችግሮችን ወደ እድል በመቀየር ጭምር በሁሉም ሴክተሮች አበረታች የሆኑ ውጤቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል።
በተለይም የ25 ዓመት አሻጋሪ የልማት እና የ5 ዓመት ስትራቴጂካዊ ዕቅዶችን ለመተግበር የተደረገው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን አንስተው በሁሉም ዘርፍ የሕዝብን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ ስኬታማ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።
የተቋማትን፣ የአመራሩንና የባለሙያውን የመፈጸም አቅም በማሳደግ የተሻለና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ በመገንባት በኩል ተስፋ የሚሰጡ ጅምሮች መኖራቸውንም አንስተዋል።
በመሆኑም የክልሉን ህዝብ ጥያቄ መሰረት በማድረግ የተጀመሩ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች በአዲሱ በጀት አመትም ይበልጥ ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን ተናግረዋል።
በአዲሱ ዓመት አዲስ መንግስት የሚመሰረትበትና ተስፋ የተሰነቀባቸው የልማት ስራዎችም በላቀ ቁርጠኝነት የሚተገበሩበት ይሆናል ብለዋል።
በተጨማሪም በየደረጃው በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ አሠራርን ተግባራዊ በማድረግ ሕዝብን የሚያረካ አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ላይ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።
ከቀደሙ ተግዳሮቶች ትምህርት በመውሰድና የተሻሉ ተሞክሮዎችን በማስፋት በአዲሱ በጀት ዓመት የሕዝብን ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ የመጠበቅና ዘርፈ-ብዙ ምርታማነትን የማሳደግ ሥራ በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል።
የክልሉን ብሎም የሀገርን ኢኮኖሚ በዘላቂነት በሚያሳድጉ ተግባራት ላይ በማተኮር ለስኬታማነቱ የተቀናጀ ጥረት የሚደረግ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመሆኑም በየደረጃው ያለው አመራር የጋራ ራዕይ ሰንቆና በተግባራት ዙሪያ ጠንካራ ተግባቦት በመፍጠር በተሻለ ቁርጠኝነት እና በጊዜ የለኝም መንፈስ መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።
ለሁለት ቀናት በሚካሄደው የምክክር መድረክ የክልሉ የተለያዩ ተቋማት አመራሮችና ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።