የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ለቀጣዩ የዲጂታል ሽግግር ጠንካራ መሠረት ጥሏል–ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ለቀጣዩ የዲጂታል ሽግግር ጠንካራ መሠረት ጥሏል–ምሁራን
ጅማ፤ነሐሴ 20/2018 (ኢዜአ)፦የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ትግበራ ለሀገሪቱ ቀጣይ የዲጂታል ሽግግር ጠንካራ መሠረት መጣሉን የጅማ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ምሁራን አስታወቁ።
የኢትዮጵያ መንግሥት በፈረንጆቹ 2020 ይፋ ያደረገው ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ፣ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት ለማፋጠንና አገልግሎቶችን ዘመናዊ ለማድረግ የተነደፈ ብሔራዊ መርሃ-ግብር ነው።
ስትራቴጂው በተለይም በግብርና፣በቱሪዝም፣ በማኑፋክቸሪንግ እና በዲጂታል አገልግሎቶች ላይ ትኩረት በማድረግ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻልና አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን መፍጠርን ዓላማ ያደረገ ነበር።
ምሁራኑ በ2025 የተከናወነው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ምዕራፍ ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበበትና በውጤታማነት የተጠናቀቀ መሆኑን ገልጸዋል።
በዋና ዋና ስኬትነት ከተጠቀሱት መካከል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስፋፋት፣ የፋይዳ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ትግበራ፣የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን በበይነ-መረብ መስጠት እና ለሚሊዮኖች የተሰጠው የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና እንደሚገኙበት ምሁራኑ ጠቁመዋል።
በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሜካኒካል ትምህርት ክፍል መምህር ሸዋንግዛው ወርቃገኘሁ፤የአገሪቱ የቴክኖሎጂ እንቅስቃሴ በስፋት እያደገ መምጣቱን ገልጸው፣ በርካታ ስኬቶች ከመመዝገባቸው ባለፈ በርካታ የዘርፉን ባለሙያዎች ማፍራት መቻሉን ጠቁመዋል።
የዲጂታል ቴክኖሎጂ መስፋፋት በተለያዩ ተቋማት የመረጃ አያያዝን ከማዘመኑ ባሻገር የአገልግሎት አሰጣጡን ማቀላጠፉን አብራርተዋል።
ይህም ዜጎች አገልግሎቶችን ያለ እንግልት እንዲያገኙ፣ እንዲሁም ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን እንዲቆጥቡ እያስቻላቸው መሆኑን አስረድተዋል።
በተለይም መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በአገልግሎት አሰጣጥና በመልካም አስተዳደር በኩል የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ አድንቀዋል።
የዲጂታል አገልግሎቶች የግልጽነት መርህን በማጠናከር ሙስናን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የጅማ ዩኒቨርሲቲ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ማዕከል ዳይሬክተር ኢንጂነር ጃርሚያ ባይሳ ናቸው።
ተቋማት መዘመናቸውና መገንባታቸው፣የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት መስፋፋቱ፣ እንዲሁም 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከምዝገባ ጀምሮ የመረጃ አያያዙ ዘመናዊና ስኬታማ መሆኑ የዲጂታል ሽግግሩ አበይት ውጤቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሆኖም የተመዘገቡት ስኬቶች በዚህ ብቻ ሳይወሰኑ በቀጣይ ይበልጥ መጠናከር እንዳለባቸው ኢንጂነር ጃርሚያ አስገንዝበዋል።
በተለይም ዲጂታል 2030 ስትራቴጂ ከግብ እንዲደርስ የተጀመሩ የዲጂታል ልማት ሥራዎች በተቀናጀ መልኩ መቀጠል እንዳለባቸው ገልጸዋል።
እንደ መሶብ የአንድ ማዕከል ያሉ የዲጂታል አገልግሎቶችን ማስፋፋት፣እንደ ኢትዮ-ኮደርስ ያሉ የቴክኖሎጂ ስልጠናዎችን ማጠናከር እና በዘርፉ በርካታ ብቁ ባለሙያዎችን ማፍራት ለቀጣዩ የዲጂታል ሽግግር ስኬት ወሳኝ መሆኑን ኢንጂነር ጃርሚያ ተናግረዋል።
የበለጸጉ ሀገራት ኢኮኖሚያቸውን ለማጠናከር ከተጠቀሙባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱ የግል ተቋማት ቴክኖሎጂን በመጠቀምና በማስፋፋት ረገድ ያደረጉት ንቁ ተሳትፎ መሆኑን የጠቀሱት ምሁሩ፤መንግሥትም የግል ተቋማትን በዘርፉ የማሳተፍ ሥራውን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አክለው ገልጸዋል።