ቀጥታ፡

ፋይዳ- ሌላው የኢትዮጵያ ዲጂታል ራዕይ የስኬት ጉዞ ማሳያ

ዓለም በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ዲጂታል ሥርዓት እየተሸጋገረች ባለችበት በአሁኑ ወቅት፣ ኢትዮጵያም ይህን ዓለም አቀፋዊ ግስጋሴ ተቀላቅላ በዲጂታል ዘርፉ እመርታ እያሳየች ትገኛለች።

በዚህም በዘመናዊ የለውጥ ጉዞ እንደ ዋና ምሰሶ የሚያገለግለው ፋይዳ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ፣ አሁን ላይ የሀገሪቱ ዲጂታላይዜሽን ስኬት ጉልህ ማረጋገጫ ለመሆን በቅቷል።

የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ የሀገሪቱን የዲጂታል ሽግግር ስራ የማገዝ እና ዘመናዊ የኢኮኖሚ መሠረተ-ልማት መገንባትን መነሻ በማድረግ በ2013 ዓ.ም በሙከራ ደረጃ ተጀምሯል።

መንግስት እያንዳንዱ ነዋሪ በአካልም ሆነ በኦንላይን ማንነቱን በተአማኒነት ማረጋገጥ የሚችልበት ሥርዓት እንደሚያስፈልግ በመረዳት የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራምን አስጀምሯል።

ፕሮግራሙ የቅድመ-ሙከራ ስራዎችን ሲጀምር ቀደም ሲል የነበሩትን የተበታተኑ፣ ለአጭበርባሪዎች የተጋለጡ እና አንዱ ድርጅት ከሌላው ጋር መረጃ የማይለዋወጥባቸውን የቆዩ አሰራሮች በአንድ ማዕከላዊ የባዮሜትሪክ ስርዓት መተካት ዋነኛ ግብ አደረገ።

ስርዓቱ ጠንካራ ህጋዊ መዋቅር እንዲኖረውም የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ አዋጅ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸደቀ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን አስመልክቶ የተለያዩ ሀሳቦችን አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፋይዳ መታወቂያን ተራ መለያ ሰነድ ብቻ ሳይሆን፣ የዜጎችን ክብርና መብት ማረጋገጫ እንዲሁም ዘመናዊ የኢኮኖሚ ነጻነትን የሚያፋጥን የሉዓላዊነት መሣሪያ አድርገው ገልጸውታል።

በተለይም በመንግስት መስሪያ ቤቶችና በግል ተቋማት ውስጥ የሚስተዋለውን የመረጃ መጭበርበር፣ አድካሚ ቢሮክራሲ እና ሙስናን ሙሉ በሙሉ በማስወገድ ረገድ ይህ ዲጂታል መሠረተ-ልማት የመፍትሔው ዋነኛ ቁልፍ መሆኑን በተደጋጋሚ አጽንኦት ሰጥተውበታል።

ይህ የፋይዳ መታወቂያ ጉዞ ከኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የዲጂታል ስትራቴጂ 2030 ራዕይ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው። ሀገሪቱ እስከ 2030 .ድረስ ሙሉ በሙሉ ወረቀት አልባ፣ የተቀናጀ የኤሌክትሮኒክስ መንግስት አሰራር የሰፈነባት እና በዲጂታል ክፍያ የምትመራ የኢኮኖሚ ማዕከል ለመሆን ያቀደችውን ግብ ለማሳካት ፋይዳ እንደ ዋና የጀርባ አጥንት ሆኖ ያገለግላል።

ማንኛውም የዲጂታል አገልግሎት፣ የኦንላይን ንግድና የኢኮኖሚ ትስስር ያለምንም እንከንና በተገቢው ፍጥነት መተግበር የሚችለው እያንዳንዱ ዜጋ ሊጭበረበር የማይችል አስተማማኝ የዲጂታል ማንነት ሲኖረው ብቻ በመሆኑ የፋይዳ ሚና ለስትራቴጂው ስኬት ወሳኝ ነው።

በአሁኑ ወቅት የፋይዳ መታወቂያ ፕሮግራም ከቀላል የፓይለት ፕሮጀክትነት ተሻግሮ፣ ወደ ትልቅ ሀገራዊ ተቋምነት ተቀይሯል። ተቋሙ ይበልጥ በራሱ እንዲንቀሳቀስና አገልግሎቱን እንዲያሰፋ «ፋይዳቨርስ» በሚል ስያሜ ራሱን የቻለ የመንግስት የልማት ድርጅት ሆኖ በይፋ ተዋቅሯል።

በዲጂታል መታወቂያ ስርዓ የተመዘገቡት ጠቅላላ የሰዎች ቁጥር ከ49 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የደረሰ ሲሆን፣ ይህም በሀገር አቀፍ ደረጃ የተዘረጉ ከ12 ሺህ በላይ የባዮሜትሪክ መመዝገቢያ መሣሪያዎችን (Registration Kits) በስፋት ጥቅም ላይ በማዋል የተመዘገበ ታላቅ ስኬት ነው።

ከተመዘገቡት ነዋሪዎች መካከልም ከ14 ነጥብ 3 በመቶ በላይ የሚሆኑት የፕላስቲክ ካርድ ህትመታቸው ተጠናቆ በቀጥታ ማግኘት ችለዋል።

ይህ የዲጂታል መታወቂያ አሰራር አሁን ላይ ከተለያዩ ዘርፎች ጋር በጥብቅ በመተሳሰር የዕለት ተዕለት አገልግሎት ማረጋገጫ እየሆነ ይገኛል።

እስከ አሁን ድረስ 150 የሚሆኑ የመንግስት እና የግል የልማት ድርጅቶች (Integrated Agencies) የአሰራር ስርዓታቸውን ከፋይዳ ጋር ያቀናጁ ሲሆን፣ ይህም ተቋማቱ የደንበኞቻቸውን ማንነት በሴከንዶች ውስጥ በዲጂታል መንገድ እንዲያረጋግጡ አስችሏቸዋል።

በዚህም ምክንያት እስከ አሁን ድረስ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ማለትም ከ194 ሚሊዮን በላይ የዲጂታል ማንነት ማረጋገጫ (eKYC) ፍተሻዎች በተሳካ ሁኔታ ተከናውነዋል።

በፋይናንስ ዘርፍ ባንኮች አዳዲስ ደንበኞችን ለመመዝገብና የቆዩ አካውንቶችን ከፋይዳ ጋር ለማገናኘት ይህንን ቴክኖሎጂ በስፋት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።

ይህ የፋይዳ ዲጂታል አሰራር በሀገሪቱ ማኅበራዊ እና ፍትሃዊ አካታችነት ላይ የሚያሳድረው በጎ ተፅዕኖ እጅግ የጎላ ነው።

ቀደም ሲል የመታወቂያ አገልግሎት ለማግኘት በጂኦግራፊያዊ ርቀት፣ በወረቀት ቢሮክራሲ ወይም በሌሎች ማኅበራዊ ምክንያቶች ይገለሉ የነበሩ ህብረተሰብ ክፍሎች በተለይም በገጠር የሚኖሩ ዜጎች፣ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች እና በሀገሪቱ የሚገኙ ስደተኞችና አሁን ላይ እኩል በሆነ መንገድ የመንግስትና የግል አገልግሎቶችን የሚያገኙበትን በር ከፍቶላቸዋል።

የዲጂታል ማንነት የዜግነት ክብርና ተደራሽነትን በማረጋገጥ፣ ማህበራዊ ፍትሕን የሚያሰፍን ሀገራዊ ድልድይ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል።

በሌላ በኩል፣ ከሀገራዊ ደህንነትና የፋይናንስ ዘርፍ ጥራት አንጻር የፋይዳ አስተዋፅኦ ወደር የለውም። የህገ-ወጥ ገንዘብ ዝውውርን (Money Laundering) እና ህገ-ወጥ ደላሎችን ለመግታት በባንኮችና በፋይናንስ ተቋማት የሚደረጉ ቁጥጥሮችን ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል ማዕቀፍ ቀይሮታል።

እያንዳንዱ የፋይናንስ እንቅስቃሴ ከተረጋገጠ ግለሰብ ማንነት ጋር ብቻ የሚገናኝ በመሆኑ፣ የኢኮኖሚው ዘርፍ ግልፅነትና ተአማኒነት እንዲኖረው አድርጓል። ይህም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት (FDI) ወደ ሀገር ውስጥ በሚገባበት ወቅት በራስ መተማመንን የሚፈጥርና ሀገሪቱን ለዓለም አቀፍ አሰራር ዝግጁ የሚያደርግ ትልቅ የቴክኖሎጂ እርምጃ ነው።

የፋይዳቨርስ የወደፊት ራዕይ ይበልጥ ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ የሆኑ የትኩረት አቅጣጫዎችን ያስቀመጠ ነው።

ተቋሙ እድሜያቸው ለምዝገባ የደረሱ ተመዝጋቢዎችን ቁጥር 90 ሚሊዮን ለማድረስ እና ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን ከወላጆቻቸው መታወቂያ ጋር አገናኝቶ የመመዝገብ ልዩ አሰራርን ለማስፋት እየሰራ ይገኛል።

ከዚህ በተጨማሪ ማንኛውንም አዲስ የባንክ አካውንት ለመክፈት፣ ሲም ካርድ ለመግዛት፣ ፓስፖርት ለማደስ፣ የመንጃና የንግድ ፈቃድ ለማውጣት የፋይዳ ቁጥርን ብቸኛ እና ግዴታ የማድረግ ሂደትን ሙሉ በሙሉ ማጠናቀቅ ዋነኛ ትኩረቱ ነው።

ተጠቃሚዎች የትኛው ተቋም የትኛውን መረጃቸውን ማየት እንዳለበት ራሳቸው መቆጣጠር የሚችሉበትን የሉዓላዊ ማንነት ቴክኖሎጂን ማጎልበት እና የግል መረጃዎችን ፍጹም ደህንነት ማረጋገጥም የስትራቴጂው አካል ነው።

በአጠቃላይ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ከጥንስሱ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያሳየው ፈጣን እድገት፣ የኢትዮጵያን የዲጂታል ጉዞ ስኬታማነት ማሳያ ነው።

ከግለሰቦች አልፎ ለባንኮች፣ ለትምህርት ተቋማት እና በሀገሪቱ ለሚኖሩ ስደተኞች ጭምር እኩል መብትና አገልግሎትን በዲጂታል መንገድ ተደራሽ እያደረገ ይገኛል።

ፋይዳ የኢትዮጵያን ዲጂታል ስትራቴጂ 2030 ራዕይን በማሳካት፣ ሁሉንም ዜጎች ያካተተ ፍትሃዊ፣ ደህንነቱ የተጠበቀና በዲጂታል ክፍያ የሚመራ ዘመናዊ የኢኮኖሚ ስርዓት ለመገንባት የሚያስችል ስትራቴጂካዊ ምሰሶ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም