ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ታምርት እና የኢንዱስትሪው ትንሳኤ

ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ሽግግር ጉዞ ውስጥ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ መዋቅራዊ ማነቆዎችን ለመፍታት፣ ምርታማነትን ለማሳደግ እና የሀገር ውስጥ ምርትን ለማዘመን የታለመ ታላቅ ሀገራዊ መርሐ ግብር ነው።

ንቅናቄው በአጭር ዓመታት ውስጥ በኢኮኖሚ ደህንነት፣ የውጭ ምርትን በሀገር ውስጥ በመተካት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ሁለንተናዊ ለውጥ አምጥቷል።

ይህ ንቅናቄ በይፋ የተጀመረው በመጋቢት ወር 2014 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አማካኝነት ነው።

የንቅናቄው አላማ በኢንዱስትሪ ዘርፉ ይስተዋል የነበረውን የቅንጅት ማጣት፣ የፋብሪካዎችን መዘጋት እና እጅግ ዝቅተኛ የነበረውን የፋብሪካዎች አማካይ የማምረት አቅም ለማሻሻል እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ እጥረትን በመቀነስ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ንቅናቄው የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ትንሣኤና የኢንዱስትሪ ሉዓላዊነት በተግባር የሚያረጋግጥ ዋና መሣሪያ ነው በማለት በተለያዩ ጊዜያት ባስተላለፏቸው መልዕክቶች ላይ ገልጸዋል።

አምራች ዘርፉን ማሳደግ የፖሊሲ ምርጫ ሳይሆን የሀገርን የኢኮኖሚ ነጻነት የማስከበር ጉዳይ መሆኑን በተደጋጋሚ አስገንዝበዋል።

የምርት ማስተዋወቅና የገበያ ትስስር ለመፍጠር ከ2015 ዓ.ም አንስቶ ሀገር አቀፍ የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ በመካሄድ ላይም ይገኛል።

አራተኛው ዙር ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ከሚያዝያ 24 እስከ ሚያዝያ 28 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል ተካሂዷል።

በዚህ ኤክስፖ ላይ ከ270 በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርቶቻቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የገበያ ትስስር ውል ተፈርሟል።

በአሁኑ ወቅት ንቅናቄው ከተጀመረ ወዲህ ተዘግተው የነበሩ ከአንድ ሺህ በላይ ፋብሪካዎች ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ የተመለሱ ሲሆን፣ ከ14 ሺህ 500 በላይ አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ እንዲሁም ከ350 በላይ አዳዲስ ግዙፍ ፋብሪካዎችም ወደ ምርት ገብተዋል።

ይህም የኢንዱስትሪዎችን አማካይ የማምረት አቅም 67 በመቶ የተሻገረ ሲሆን፣ የሀገር ውስጥ አምራቾች የምርት ድርሻም ከ30 በመቶ ወደ 45 በመቶ አድጓል።

ከፋይናንስና ከምርት ዕድገት ባሻገር፣ ንቅናቄው ብዙ ቁጥር ላላቸው ዜጎች፣ በተለይም ለወጣቶችና ለሴቶች ዘላቂ የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል።

በተጨማሪም ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር በተደረገ ቅንጅት የኢንዱስትሪዎችን የቴክኖሎጂ ፍላጎት የሚያሟላ የሰለጠነ የሰው ኃይል የማፍራት ሥራ ጎን ለጎን እየተከናወነ ይገኛል።

በ2018 በጀት ዓመት የውጭ ምርትን በሀገር ውስጥ በመተካት ረገድ የኢንዱስትሪ ምርቶችን፣ አልባሳትን እና የግብርና ማቀነባበሪያ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት እስካሁን ድረስ ከ3.5 ቢሊዮን በላይ የአሜሪካ ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳን ተችሏል። ከንቅናቄው መጀመር አንስቶ በየዓመቱ በሚዘጋጁት የገበያ ትስስሮችም በአምራቾች እና በገዢዎች መካከል ከ70 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ውል ተፈጽሟል።

የሀገር ውስጥ ምርቶችን ተወዳዳሪ ለማድረግ በኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስትቲዩትና በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አማካኝነት ለአምራቾች የቴክኒክና የሎጅስቲክስ ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል።

ይህም የሀገር ውስጥ ምርቶች በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ገበያዎች ዘንድ ያላቸው ተቀባይነትና እምነት እንዲጨምር አድርጓል።

ወደፊት የመንግስት ትኩረት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የኢንዱስትሪ መንደሮችና የረጅም ጊዜ ብድር ማመቻቸት ላይ ያተኩራል።

ለመንግስት ሰራተኞች የሚቀርቡ አልባሳት፣ ደብተሮችና የቢሮ ቁሳቁሶች በመቶ በመቶ ከሀገር ውስጥ አምራቾች እንዲገዙ የሚያስገድደው አሰራር ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን፣ ምርቶችን በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) ገበያ ላይ ተወዳዳሪ ማድረግ የወደፊቱ ዋና አቅጣጫ ነው።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከመሸመት ወደ ማምረት እና ከጥገኝነት ወደ ራስን መቻል የተደረገ ትልቅ የኢኮኖሚ አብዮት በመሆኑ፣ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚዋ የማኑፋክቸሪንግ እና የኢንዱስትሪ ማዕከል እንደሚያደርጋት ጥርጥር የለውም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም