ቀጥታ፡

ማንችስተር ዩናይትድ ለአመታት ሲፈልገው የነበረውን ካርሎስ ባሌባን አስፈረመ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 19/2018 (ኢዜአ)፦ ማንችስተር ዩናይትድ  የካሜሮኑን አማካይ ካርሎስ ባሌባን ከብራይተን በ70 ሚሊዮን ፓውንድ  ማስፈረሙን ዛሬ አስታውቋል። 

የ22 ዓመቱ ተጫዋች በኦልድ ትራፎርድ ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የሚያቆየውን ኮንትራት የተፈራረመ ሲሆን፣ እስከ እ.አ.አ 2031 በሚቆየው በዚህ ውል ላይ የክለቡ ተጨማሪ የ12 ወራት የማራዘም አማራጭ ተካቷል።

ባሌባ ወደ አዲሱ ክለቡ መቀላቀሉን አስመልክቶ በሰጠው አስተያየት፣ ለረጅም ጊዜ ለመቀላቀል ሳልመው በነበረው ማንችስተር ዩናይትድ መፈረም በመቻሌ ታላቅ ደስታና ክብር ይሰማኛል ብሏል። 

ከአሰልጣኝ ማይክል ካሪክ ጋር በመስራት እና የእሱን ልምድ በመጠቀም ብቃቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ እንደሚፈልግም ገልጿል።

ባሌባ በማንችስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ማይክል ካሪክ ስር በክረምቱ የዝውውር መስኮት የፈረመ ሶስተኛው የአማካይ  ተጫዋች ሆኗል። 

ዩናይትድ ቀደም ሲል አንድሬ ሳንቶስን ከቼልሲ በ48 ሚሊዮን ፓውንድ እና ዩሪ ቲሊማንስን ከአስቶንቪላ በ35 ሚሊዮን ፓውንድ ማስፈረሙ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም