ማዕከላቱ በሽታና ሙቀትን የሚቋቋሙ የስንዴ ዝርያዎችን በማውጣት የአርሶና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት እያሳደጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ማዕከላቱ በሽታና ሙቀትን የሚቋቋሙ የስንዴ ዝርያዎችን በማውጣት የአርሶና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት እያሳደጉ ነው
አዳማ፤ ነሐሴ 19/2018 (ኢዜአ)፡-የግብርና የምርምር ማእከላት በቆላማ አካባቢዎች በሽታና ሙቀትን የሚቋቋሙ የስንዴ ዝርያዎችን በምርምር በማውጣት የአርሶና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት እያሳደጉ መሆናቸውን የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ገለጸ።
ብሔራዊ የዘር ብዜትና አጠቃቀም የአሰልጣኞች ሥልጠናና የባለድርሻ አካላት ምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ንጉሤ ደቻሳ እንዳሉት፤ የግብርና ምርምር ማዕከላት የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ፣ በማስተዋወቅ እንዲሁም ዘርን በማባዛት ለግብርና ምርትና ምርታማነት ማደግ ከፍተኛ ድርሻ እያበረከቱ ይገኛሉ።
ለዚህም ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር በቆላማ አካባቢዎች በሽታና ሙቀትን የሚቋቋሙ የስንዴ ዝርያዎችን በምርምር በማፍለቅና ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች በማቅረብ ረገድ ያደረጉት ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
የስንዴ ሰብሎቹም በቆላማ አካባቢዎች በሽታንና ሙቀትን በመቋቋም የአርሶና ከፊል አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚነት ማሳደጋቸውን አስታውቀዋል።
በዚህ ረገድ የአፍሪካ የግብርና ቴክኖሎጂ ማሸጋገሪያ ፕሮጀክት የመስኖ ስንዴ ቴክኖሎጂዎችን የማቅረብ እና መነሻ ዘሮችን የማባዛት ሥራን ሲደግፍ መቆየቱን ጠቁመዋል።
በኢንስቲትዩቱ የፕሮጀክቱ አስተባባሪና የቁሉምሳ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ዓለማየሁ በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ ተግባራዊ በተደረገባቸው በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና በአፋር ክልሎች የስንዴ ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ አዎንታዊ ውጤት ማስገኘቱን ተናግረዋል።
በዚህም የአርሶ አደሩን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም በማሻሻል አማካይ የስንዴ ምርትና ምርታማነትን በሄክታር 40 ኩንታል ማድረስ መቻሉንም አስረድተዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ደጀኔ ሂርጳ፤ ከግብርና ምርምር የሚወጡ የስንዴ ዝርያዎች በሽታን የመቋቋም አቅማቸውና ምርታማነታቸው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
በፕሮጀክቱ ተሻሽለው የወጡ አዳዲስ ዝርያዎች በክልሉ በሄክታር የሚገኘውን ምርት 40 ኩንታል ማድረሳቸውንም አስረድተዋል።
ከፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች መካከል በአርሲ ዞን የሄጦሳ ወረዳ አርሶ አደር አበራ ደገፋ በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ የስንዴ ቴክኖሎጂን ተደራሽ በማድረጉ ምርታማነታቸውን በእጥፍ ማሳደግ እንደቻሉም ተናግረዋል።