ቀጥታ፡

የአፍሪካን የጤና ሥርዓት ከጥገኝነት ለማላቀቅ ከቃል ኪዳን የተሻገረ ቁርጠኛ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል - ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 19/2018 (ኢዜአ)፦የአፍሪካን የጤና ሥርዓት ከጥገኝነት ለማላቀቅ ከቃል ኪዳን የተሻገረ ቁርጠኛ የባለቤትነት እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ ገለጹ።

በአምስት የጤና ዘርፍ ምሰሶዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ለአራት ቀናት የሚቆየው 76ኛው የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣናዊ ኮሚቴ ጉባኤ በአዲስ አበባ የአድዋ ድል መታሰቢያ መካሄድ ጀምሯል። 


 

የመድረኩ ዋና ዋና የጤና ምሰሶዎች ዘላቂ የጤና ፋይናንስና የዲጂታል ጤና ሥርዓት፣ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤ፣ እንዲሁም የጤና ባለሙያዎችና የሀገር ውስጥ ምርቶች አቅም ማሳደግ ናቸው።

ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በዓለም አቀፍ ተለዋዋጭ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ተግዳሮቶች ምክንያት በዜጎች ጤና ስርዓት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደሩ ይገኛሉ።

በዚህም አፍሪካ የዜጎቿን የጤና አጠባበቅ ስርዓት በማዘመን በተለዋዋጭ ዓለም አቀፍ ሁኔታ የሚደርስን የጤና ተጋላጭነት በራስ አቀም ምላሽ መስጠት እንዳለባት ተናግረዋል።

እነዚህ ተግዳሮቶች አፍሪካ ቀጣናዊ ትብብር ውስጥ የጋራ ድምጿን ለማጠናከርና በጤና ጉዳዮቿ ላይ ሙሉ ባለቤትነትን ለመያዝ ታሪካዊ ዕድል እንደሚፈጥሩ ገልጸዋል።

አፍሪካ በግልጽና በደፋር አቅጣጫ የተመሠረተ የተቀናጀ የጋራ ስትራቴጂ እንደሚያስፈልጋት በመጠቆም፤ በጤና ላይ የምታደርገውን የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንት ማሳደግ እንዳለባትም አስታውቀዋል።

የአህጉሪቷን የጤና ስርዓት ለማዘመንም ስትራቴጂክ አጋርነት በማጠናከር የጤና ደኅንነት የራስ መድኃኒቶች፣ ክትባቶችና የምርመራ መሣሪያዎች ማምረትን እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል።

በዓለም ጤና ድርጅትና በአፍሪካ የበሽታ ቁጥጥርና መከላከያ ማዕከል መካከል ተግባራዊ ቅንጅት በማጠናከር በጉባኤው የሚተላለፉ ውሳኔዎችን ከአጀንዳ 2063 ግብ ጋር አቆራኝቶ መተግበር ያስፈልጋል ብለዋል።


 

ኢትዮጵያ ጤናን እንደ ስትራቴጂካዊ ብሔራዊ ኢንቨስትመንት በመቁጠር በራስ አቅም የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር አቅሟን ከጊዜ ወደጊዜ እያጎለበተች እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የጤና ሥርዓቱን ለማሻሻልና ለማስፋት የተከናወኑ ተግባራትም በእናቶች፣ ሕፃናትና ልጆች ላይ የሚከሰትን በሽታ የመከላከልና የመቆጣጠር አቅም ማጎልበቱን ተናግረዋል።

የአፍሪካ ቀጣዩ የጤና ምዕራፍ ከጥገኝነት ይልቅ ባለቤትነትን፣ ከመበታተን ይልቅ ውህደትን፣ ከቃል ኪዳን ይልቅ ተግባራዊ እርምጃን የሚያስቀድም መሆን እንዳለበት አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ ቀጣናዊና አሕጉራዊ የጤና ኢንቨስትመንት አቅምን ለማጎልበት በሚደረገው ጥረት ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ቁርጠኛ አቋም እንዳላት አረጋግጠዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም