ቀጥታ፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከልጆች ኢንቨስትመንት ፈንድ ፋውንዴሽን መስራች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 19/2018 (ኢዜአ)፦ የልጆች ኢንቨስትመንት ፈንድ ፋውንዴሽን መስራች ክሪስን በለነገዋ ጋር በቀጣይ በጋራ በሚሰሩባቸው ስራዎች ዙሪያ መወያየታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የልጆች ኢንቨስትመንት ፈንድ ፋውንዴሽን (CIFF) መስራች እና የቦርድ ሃላፊ ክሪስ ሆን እና ቡድናቸውን ለነገዋ የሴቶች የተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከልን ማስጎብኘታቸውንም ገልጸዋል።

ለነገዋ ጅማሮው በተለያዩ ማህበራዊ ችግር ውስጥ ያሉ ሴት እህቶቻችን ተስፋና እድላቸው እዲለመልም፣ ክብራቸውና ደህንነታቸው ተጠብቆ የተሻለ ሕይወት እንዲመሩ ከልብ በመነጨ ስሜት የተፀነሰ፣ ተፀንሶም ወደ ተግባር የተቀየረ ትልቅ ራዕይን የሰነቀ ስራ ነው ብለዋል።


 

የእነዚህ እህቶቻችንን ህይወት ለመቀየር፣ ለነገዋ የሴቶች የተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ከ2016 ዓ.ም ጀምረነው በ5 ዙር በተለያዩ የሙያ ዘርፎች 3 ሺህ 259 ሰልጣኞችን በክህሎት እና በስብዕና ግንባታ አሰልጥነን ወደ ስራ አሰማርተናል ሲለም ገልጸዋል።

ዛሬ ሁሉም ተመራቂዎች ክብር ያለው ኑሮ፣ ብሩህ ተስፋን ሰንቀው አዲስ ህይወት መኖር ጀምረዋል ብለዋል።

“ከምንሰራቸው ስራዎች ሁሉ ትልቁ ስራ በሰው ላይ የምንሰራው፣ በተለይም በሴቶች ላይ የምንሰራው ነው” የሚለውን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መልዕክት የስራችን ማዕከል አድርገን እየፈፀምን እንገኛለን ነው ያሉት።

በከተማችን ላይ ከሚታየው ለውጥ ሁሉ የሚልቀው በለነገዋ ሴቶች ላይ እያየን ያለው ለውጥ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ለ”ለነገዋ የተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል” የሰነቅነው ራዕይ፣ በዓመት እስከ 10 ሺህ ሴቶችን የሚያበቃ፣ እንዲሁም አካታች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ልምድ የሚቀሰምበት የልህቀት ማዕከል እንዲሆን ማስቻል መሆኑንም ጠቅሰዋል።


 

ይህ ራዕይ በተሟላ ሁኔታ እንዲተገበር ሊደግፋን የመጡት የልጆች ኢንቨስትመንት ፈንድ ፋውንዴሽን (CIFF) መስራች ክሪስን በለነገዋ የሴቶች የተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል የምንሰራቸው ሰው ተኮር ስራዎች አስጎብኝተን በቀጣይም በጋራ በምንሰራቸው ስራዎች ዙሪያ ተወያይተናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም