ቀጥታ፡

የአፍሪካ ሀገራት የጤና ተደራሽነትና ዘላቂነትን የሚያረጋግጡ አቅሞችን መገንባት ይጠበቅባቸዋል - መሐሙድ አሊ ዩሱፍ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 19/2018 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካ አባል ሀገራት የዜጎቻቸውን የጤና አገልግሎት ተደራሽነትና ዘላቂነት የሚያረጋግጡ አቅሞችን መገንባት እንደሚጠበቅባቸው የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ገለጹ።

በአምስት የጤና ዘርፍ ምሰሶዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ለአራት ቀናት የሚቆየው 76ኛው የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣናዊ ኮሚቴ ጉባኤ በአዲስ አበባ የአድዋ ድል መታሰቢያ መካሄድ ጀምሯል።


 

የመድረኩ ዋና ዋና የጤና ምሰሶዎችም ዘላቂ የጤና ፋይናንስና የዲጂታል ጤና ሥርዓት፣ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤ፣ እንዲሁም የጤና ባለሙያዎችና የሀገር ውስጥ ምርቶች አቅም ማሳደግ ናቸው።

በዚሁ ወቅት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ ጨምሮ የአፍሪካ አባል ሀገራት መንግሥታት ከፍተኛ ሥራ ኃላፊዎች፣ የልማት አጋሮች እንዲሁም ቀጣናዊና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሥራ መሪዎች ታድመዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ በዚሁ አጋጣሚ እንዳሉት፤ ሁሉንም አማራጮች በመጠቀም የአህጉሪቱን የጤና ሉዓላዊነት ማረጋገጥ ቀጣይነት ያለው ተግባር ይጠይቃል።

የአፍሪካን ጤና ሥርዓት ዘላቂነት በአስተማማኝ መሠረት ለመገንባት የፋይናንስ አቅምን በማጎልበት የምርምርና ፈጠራ አቅሞችን ማሳደግ እንደሚገባም አመላክተዋል።


 

የዘንድሮው የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ ጭብጥ አፍሪካውያንን የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ለማሻሻል በውሃና ንፅህና አጠባበቅ ላይ ትኩረት ማድረጉን ገልጸዋል።

የአህጉሪቱ አባል ሀገራትም የዜጎቻቸውን የጤና ሥርዓት የሚያሻሽሉ የፋይናንስ፣ የሰው ኃይልና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በራስ አቅም ማቋቋም ባህል ማዳበር እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የአህጉሪቱን የጤና ሥርዓት ለማሻሻል ከአባል ሀገራት፣ የልማት አጋሮችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።

በቀጣይም ከዓለም ጤና ድርጅትና ከልማት አጋሮች ጋር በመተባበር የአህጉሪቱን የጤና ሥርዓቶች በተቀናጀ ዕቅድ ለመምራት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

በጉባኤው የሚደረጉ ውይይቶችና የሚወሰኑ ውሳኔዎች ለአፍሪካ የጤና ሉዓላዊነት፣ ራስን መቻልና ዘላቂ የጤና ሥርዓት ግንባታ ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም