በዞኑ የትምህርት ጥራትንና ተሳትፎን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የትምህርት ጥራትንና ተሳትፎን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል
ገንዳ ውኃ፣ ነሐሴ19/2018 (ኢዜአ):- በምዕራብ ጎንደር ዞን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የትምህርት ጥራትንና ተሳትፎን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን የዞኑ አስተዳደር ገለጸ።
የዞኑ ትምህርት መምሪያ በበኩሉ በትምህርት ዘመኑ ከ152 ሺህ በላይ ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጿል።
በዞኑ የተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማና የ2019 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የተማሪ ምዝገባ ንቅናቄ መድረክ በዛሬው ዕለት በገንዳ ውኃ ከተማ ተካሄዷል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እያሱ ይላቅ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የትምህርት ጥራትንና ተሳትፎን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል።
የተገኙ ተሞክሮዎችን በመቀመርና ችግሮችን በማረም በአዲሱ የትምህርት ዘመን የሚመዘገቡ ተማሪዎችን ሙሉ በሙሉ መዝግቦ ለማስተማር ዝግጅት መደረጉንም ገልጸዋል።
በዞን፣ በወረዳና በከተማ አስተዳደር ደረጃ ያለው አመራርም ለትምህርት ምዝገባ ሥራው ልዩ ትኩረት በመስጠት የተያዘውን ግብ ለማሳካት መረባረብ እንዳለበትም አሳስበዋል።
የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ አያና በበኩላቸው፤ በዞኑ በአዲሱ የትምህርት ዘመን ከ152 ሺህ በላይ ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል።
በተጀመረው የሙከራ ምዝገባ በሰባት ቅድመ-አንደኛ ደረጃ እና በዘጠኝ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ዕቅዱን 100 በመቶ ማሳካት መቻሉን አስረድተዋል።
ይህም ተማሪዎችን በወቅቱ ትምህርት በማስጀመር የትምህርት ተደራሽነትን፣ ጥራትንና አግባብነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
በክረምት ወራቱም የትምህርት ቤቶች ጥገናን፣ መሠረተ ልማትን ማሟላትና ውብና ማራኪ ማድረግን የመሳሰሉ ተግባራትን በማከናወን የተሳካ የትምህርት አጀማመር እንዲኖር እየተሠራ መሆኑንም አክለዋል።
የቀጣይ ትውልድ ግንባታ መሠረት የሆነውን ትምህርት ለማጠናከር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ እንዳለ ማሩ ናቸው።
በዚህም ባለድርሻ አካላት የትምህርት ቤቶችን የመሠረተ ልማትና የግብዓት እጥረቶች ለመቅረፍ እንዲሁም አንድም ተማሪ ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይቀር የማድረግ ተግባርን በኃላፊነት ሊተገብሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በዞኑ የተማሪዎች ምዝገባን እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2018 ዓ.ም በማጠናቀቅ ትምህርትን በወቅቱ ለማስጀመር እየተሠራ መሆኑም ተመልክቷል።
በመድረኩም የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች፣ የትምህርት ቤተሰቦች፣ ርዕሳነ መምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።