ቀጥታ፡

ሙስሊሙ ማህበረሰብ በዓሉን ሲያከብር ከሐይማኖቱ አስተምህሮ በመነሳት ለሰላምና ልማት የድርሻውን በመወጣት ሊሆን ይገባል

ድሬደዋ፣ ነሐሴ 19/2018 (ኢዜአ)፡-ሙስሊሙ ማህበረሰብ በዓሉን ሲያከብር ከሐይማኖቱ አስተምህሮ በመነሳት ለሰላምና ልማት የድርሻውን በመወጣት ሊሆን እንደሚገባ ተገለጸ።

በድሬዳዋ  1 ሺህ 501ኛው የነቢዩ መሐመድ የልደት በዓል (መውሊድ) በደመቀ ሁኔታ ተከብሯል።


 

በድሬደዋ ሁለገብ የወጣቶች ማዕከል በተከበረው በዓል ላይ የነቢዩ መሐመድን አስተምህሮ መሠረት ያደረጉ ትምህርቶችና ውይይቶች ተካሄደዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የድሬደዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ በወቅቱ እንዳሉት፤ የነቢዩ መሐመድ የልደት በዓል የአንድነት፣ የመደጋገፍ፣ የሰላምና የፍቅር በዓል ነው።

ሙስሊሙ ማህበረሰብ በዓሉን ሲያከብር ከሐይማኖቱ አስተምህሮ በመነሳትና የተማረውን በመተግበር ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ልማት የድርሻውን በመወጣት ሊሆን ይገባል ብለዋል። 

በተለይም እንደ ሀገር የተጀመረውን የሀገረ መንግሥት ግንባታና ችግሮችን በውይይትና በመነጋገር የመፍታት ባህልን በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል። 


 

የድሬደዋ አስተዳደር የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ሼህ ከድር አሊ በበኩላቸው፤ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ የነቢዩ መሐመድ የመውሊድ በዓልን የሚያከብረው አንድነትን፣ ሰላምንና ፍቅርን በሚያጠናክሩ ተግባራት መሆኑን ገልጸዋል። 

በተለይም በዓሉ የአንድነት፣ የመረዳዳት፣ የመደጋገፍ፣ የፍቅርና ዘላቂ ሕብረት የሚጠናከርበት መሆኑን ገልጸዋል። 

ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ለሀገርና ለድሬዳዋ ሁለንተናዊ ሰላም፣ ልማትና እድገት እያበረከተ የሚገኘውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥልም አስገንዘበዋል።


 

በበዓሉ ላይ ከተገኙት ምዕመናን መካከል ወይዘሮ ሰብረን ኢምራን፣ የነቢዩ መሐመድ የመውሊድ በዓል የሚከበረው በድሬደዋ የሚገኙ ችግረኞችን በመደገፍና በመርዳት እንደሆነ ተናግረዋል።


 

ወጣት አባስ አብደላ እና ወጣት አስማ ረፊቅ በበኩላቸው፣ በዓሉ ወጣቶች የእርስ በርስ ፍቅርና አንድነትን የሚያጠናክሩበት መሆኑን ገልጸዋል። 


 

ወጣቶቹ አክለውም ለሀገር እድገትና ለአካባቢያቸው ዘላቂ ሰላም እየተወጡ የሚገኙትን ኃላፊነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም