የመውሊድ በዓልን ያለንን በማካፈልና አቅመ ደካሞችን በመደገፍ እያከበርን እንገኛለን - የዕምነቱ ተከታዮች - ኢዜአ አማርኛ
የመውሊድ በዓልን ያለንን በማካፈልና አቅመ ደካሞችን በመደገፍ እያከበርን እንገኛለን - የዕምነቱ ተከታዮች
ሀዋሳ ፤ነሀሴ 19/2018 (ኢዜአ)፦ የመውሊድ በዓልን ያለንን በማካፈልና አቅመ ደካሞችን በመደገፍ እያከበርን ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሀዋሳ ከተማ የእስልምና እምነት ተከታዮች ተናገሩ።
1 ሺህ 501 ኛው የነቢዩ መሐመድ ልደት የመውሊድ በዓል በሀዋሳ ከተማ በተለያዩ ሀይማኖታዊ ኩነቶች እየተከበረ ነው፡፡
ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የእስልምና እምነት ተከታዮች እንደገለፁት፤ የመውሊድ በዓልን ያለንን በማካፈልና አቅመ ደካሞችን በመደገፍ እያከበርን እንገኛለን፡፡
ወይዘሮ ፋጤ ናሥር የከተማው ነዋሪ ሲሆኑ በራህማ መስጂድ በመገኘት ማዕድ በማጋራትና ሌሎች ሐይማኖታዊ ትውፊቶችን በመፈፀም እያከበሩ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡
ከቤተሰቦቻቸው ጋር ከሚያከብሩት ባልተናነሰ በመስጂድ በመገኘት ከሌሎች ጋር በጋራ በመሆንና ያላቸውን በማካፈል የሚያሳልፉት የበዓል አከባበር እንደሚያስደስታቸው ገልፀዋል።
ወጣት ሀምዛ ከድር በበኩሉ በዓሉን ከሌሎች ወጣቶች ጋር በመሆን አቅመ ደካሞችን በመደገፍና ማዕድ በማጋራት እንዲሁም የበጎ ተግባር መርሀ ግብሮችን በማስተባበር እያሳለፈ መሆኑን አስረድቷል።
መደጋገፍና በአብሮነት በዓልን ማሳለፍ ከአባቶቻችን የወረስነው ነው ያለው ወጣት ሀምዛ ይህም ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንሰራለን ብሏል።
የመውሊድ በዓል ከሌሎች በዓላት በተለየ መልኩ በመስጂድ በመሰባሰብ በአንድ ላይ የምናከብረው በመሆኑ ልዩ ድባብና ድምቀት አለው ያለችው ደግሞ ወጣት ሀያት ኢድሪስ ናት።
አክላም የአብሮነትና የመረዳዳት እሴቶቻችንን አጠናክረን ማስቀጠል ላይ ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል ብላለች።
በሀዋሳ ከተማ የሐይማኖት መምህር የሆኑት ሀጂ አብዱልፈታ ያሲን በበኩላቸው በእርስ በእርስ መተሳሰብ፣ ያለው ለሌለው በማካፈል እና ከሁሉም ጋር በአብሮነት መኖር የነቢዩ መሐመድ የአስተምህሮ መንገድ ነው ብለዋል፡፡
እኛም አስተምህሮውን ተከትለን ያለንን በማካፈልና በዓሉን በጋራ በማክበር ሐይማኖታችን የሚያዘንን እየፈፀምን እንገኛለን ነው ያሉት፡፡
የነቢዩ የመተሳሰብና የሠላም አስተምህሮ በአንድነት ተከባብሮ ለመኖር የሚያበረክተው አስተዋፅዖ የጎላ ነው ያሉት ሀጂ አብዱልፈታ ይህንኑ ለልጆቻችን ለማስተላለፍ የማስተማር ሥራ እየሰራን ነው ብለዋል፡፡