ቀጥታ፡

የመውሊድ በዓልን ፍቅርን፣ ሰላምንና አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ እያከበርን ነው- የእምነቱ ተከታዮች

ወልቂጤ ፤ ነሐሴ 19/2018 (ኢዜአ)፦የመውሊድ በዓልን ፍቅርን፣ ሰላምንና አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ እያከበሩ መሆኑን በወልቂጤ የእምነቱ ተከታዮች ገለጹ።

የ1501ኛው የመውሊድ በዓል በወልቂጤ ከተማ በተለያዩ ሃይማኖታዊ እና አብሮነትን በሚያጠናክሩ ሥነ ሥርዓቶች በመከበር ላይ ይገኛል።


 

የወልቂጤ ከተማ የእምነቱ ተከታዮች የመውሊድ በዓልን ፍቅርን፣ ሰላምንና አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ እያከበሩ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ ሳላህዲን ሚፍታ፤ "የመውሊድ በዓል የፍቅር፣ የሰላም እና የአንድነት መገለጫ በመሆኑ በአብሮነትና በመደጋገፍ በደስታ እያከበርነው ነው" ብለዋል። 

በአብሮነት የመኖር እሴቶችን በተግባር ለማሳየት በዓሉን ከቤተሰቦቻቸውና ከጎረቤቶቻቸው ጋር በጋራ ተሰባስበው እያከበሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

አቶ ሲራጅ ጀማል በበኩላቸው ነቢዩ መሐመድ ለሰው ልጆች ያሳዩትን የመተዛዘንና የመረዳዳት እሴት በመከተል ትስስርን በሚያጠናክር መልኩ በዓሉን እያከበሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። 


 

በዓሉን ምክንያት በማድረግ የአካባቢያቸው ነዋሪዎችን በማስተባበር ሕፃናት እና አቅመ ደካማ ወገኖች የደስታው ተካፋይ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ እየሠሩ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የመውሊድ በዓልን ሃይማኖታዊ አስተምህሮውን በጠበቀ መልኩ በድምቀት እያከበሩ እንደሚገኙ የተናገረው ደግሞ ሌላው የበዓሉ ታዳሚ ወጣት ጠሃ ሳኒ ነው።


 

በዓሉን ያላቸውን በማካፈል፣ በመረዳዳትና አንድነትን በማጠናከር የነቢዩ መሐመድን መልካም ተግባራት በማስታወስ እያከበሩት እንደሚገኙም አመልክቷል።

በዛሬው ዕለትም የፍቅርና የአንድነት እሴቶችን በሚያጠናክር መልኩ በዓሉን እያከበሩ መሆናቸውን የጠቆመው ሌላው አስተያየት ሰጪ ረፊቅ ሙሳ፤ በዓሉ የአብሮነት እሴትን ለማጎልበት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም አመልክቷል።


 

በወልቂጤ ከተማ የነቢዩ መሐመድ የልደት በዓል በዱዓ፣ በመንዙማና በማዕድ ማጋራት መርሃ ግብሮች በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም