በክልሉ የእንስሳት ዝርያን በማሻሻል የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት ተመዝግቧል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የእንስሳት ዝርያን በማሻሻል የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት ተመዝግቧል
አርባምንጭ፤ ነሐሴ 19/2018 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የእንስሳት ዝርያን በማሻሻል የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት መመዝገቡን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ፡፡
"የእንስሳት ዝርያን ማሻሻል ለላቀ ብልጽግና" በሚል መሪ ሃሳብ በክልሉ የ2019 በጀት ዓመት የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ስራ ማስጀመሪያ ስነ ስርአት በጋሞ ዞን ዲታ ወረዳ ተካሂዷል።
በስነ ስርአቱ ላይ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) እንደገለጹት በክልሉ የእንስሳት ዝርያን በማሻሻል ምርታማነትን በማሳደግ በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት ተመዝግቧል፡፡
በክልሉ የእንስሳት ምርታማነት በመጨመሩም የምግብ ሉዐላዊነትን ለማረጋገጥ አቅም መፍጠሩን አመልክተዋል።
በክልሉ ሰፊ የእንስሳት ሀብት መኖሩን የጠቀሱት መሪሁን ( ዶ/ር ) የእንስሳት ሀብትን በአግባቡ በመንከባከብ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማላቅ የሚከናወኑ ተግራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡
የእንስሳትን ዝርያ ማሻሻል ስራው በወተት ሀብትና በዝርያ ላይ ከፍተኛ ለውጥ የሚያስገኝ መሆኑን ጠቅሰው የክልሉን አርሶና አርብቶ አደር ተጠቃሚነት ለማሳደግ በሚከናወኑ ተግባራት ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምስ አድማሱ (ዶ/ር) የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በዞኑ የምግብ ሉዐላዊነት እንዲረጋግጥ ትልቅ ፋይዳ እያስገኘ ነው ብለዋል።
በዞኑ የወተት ምርታማነት በመጨመሩ ማህበረሰቡ ጥሪት ከማፍራት ባለፈ የአመጋገብ ስርዓቱ ላይ ጉልህ ለውጥ ማሳየቱን ጠቅሰዋል።
እንደ ክልል የተጀመረውን የእንስሳት ዝርያ በማሻሻል ምርታመነትን የማሳደግ መርሃ ግብር በሁሉም ወረዳዎችና ቀበሌዎች ተግባራዊ ለማድረግ በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።
በዞኑ በሁሉም አካባቢ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ለማስፋፋት በተከናወኑ ተግባራት 500 የወተት መንደሮች ተፈጥረዋል ያሉት ደግሞ የጋሞ ዞን ግብርና መምሪያ ሃላፊ ማጌሶ ማሾሌ ናቸው።
የእንስሳት ዝርያን በማሻሻል የህዝቡን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ አመላክተዋል።