የመውሊድ በዓልን በአብሮነትና የተቸገሩትን በመርዳት እያከበርን ነው - የእምነቱ ተከታዮች - ኢዜአ አማርኛ
የመውሊድ በዓልን በአብሮነትና የተቸገሩትን በመርዳት እያከበርን ነው - የእምነቱ ተከታዮች
ሳውላ፤ ነሐሴ 19/2018 (ኢዜአ) ፡-የመውሊድ በዓልን በአብሮነትና የተቸገሩትን በመርዳት እያከበሩ መሆኑን በጎፋ ዞን ሳውላ ከተማ የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች ገለጹ።
1ሺህ 501ኛው የመውሊድ በዓል በሳውላ ከተማ በተለያዩ ሀይማኖታዊ ስርአቶች እየተከበረ ይገኛል።
ከሀይማኖቱ ተከታዮች መካከል ሼህ መሐመድ ዳውድ ለኢዜአ እንደገለጹት በዓሉን የነቢዩ መሐመድ አስተምህሮን በመከተል እያከበሩ ነው።
በዓሉን በመተሳሰብ፣ የተቸገሩ ወገኖቹን በመርዳትና ለሀገር ሰላምና አንድነት በመፀለይ እያከበሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ነብዩ መሐመድ ያስተማሩትን ሰላም፣ ፍቅርና አንድነትን በማስተማርና አርዓያ በመሆን ማክበር እንደሚገባም አመልክተዋል።
በአሉን በአብሮነትና የተቸገሩትን በመርዳት በደስታ እያከበርን ነው ያሉት ደግሞ የሳውላ ከተማ ነዋሪ አቶ መሐመድ ሲራጅ ናቸዉ።
በዓሉን ህሙማንን በመጠየቅና አቅም የሌላቸውን ወገኖች በመርዳት እያከበርን እንገኛለን ብለዋል።
አቶ አህመድ ሐሰን በበኩላቸዉ የመውሊድ በዓልን የነቢዩ መሐመድ አስተምህሮን በመከተል በአብሮነት፣ በፍቅርና በሰላም እያከበሩ መሆናቸውን ተናግረዋል ።