በአፍሪካ የጤና ሥርዓትን ለማዘመን የሀገራትን ስትራቴጂካዊ ትብብር ማጠናከር ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ የጤና ሥርዓትን ለማዘመን የሀገራትን ስትራቴጂካዊ ትብብር ማጠናከር ወሳኝ ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 19/2018 (ኢዜአ)፦ በአፍሪካ የጤና ሥርዓትን ለማዘመን በሚደረገው ጥረት የሀገራትን ስትራቴጂካዊ ትብብር የበለጠ ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ ገለጹ።
76ኛው የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ኮሚቴ ጉባኤ በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ይገኛል።
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በዓለም አቀፍ ተለዋዋጭ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ተግዳሮቶች ምክንያት በዜጎች ጤና ስርዓት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደሩ ይገኛሉ።
በዚህም አፍሪካ የዜጎቿን የጤና አጠባበቅ ስርዓት በማዘመን በተለዋዋጭ ዓለም አቀፍ ሁኔታ የሚደርስን የጤና ተጋላጭነት በራስ አቅም ምላሽ መስጠት እንዳለባት ተናግረዋል።
እነዚህ ተግዳሮቶች አፍሪካ ቀጣናዊ ትብብር ውስጥ የጋራ ድምጿን ለማጠናከርና በጤና ጉዳዮቿ ላይ ሙሉ ባለቤትነትን ለመያዝ ታሪካዊ ዕድል እንደሚፈጥሩ ገልጸዋል።
አፍሪካ በግልጽና በደፋር አቅጣጫ የተመሠረተ፣ የተቀናጀ የጋራ ስትራቴጂ እንደሚያስፈልጋት ጠቁመው፤ በጤና ላይ የምታደርገውን የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንት ማሳደግ እንዳለባትም አስታውቀዋል።
የአህጉሪቷን የጤና ስርዓት ለማዘመንም ስትራቴጂክ አጋርነት በማጠናከር የጤና ደኅንነት የራስ መድኃኒቶች፣ ክትባቶችና የምርመራ መሣሪያዎችን ማምረትን እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል።
በዓለም ጤና ድርጅት እና በአፍሪካ የበሽታ ቁጥጥርና መከላከያ ማዕከል መካከል ተግባራዊ ቅንጅት ማጠናከር ይገባል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ በጉባኤው የሚተላለፉ ውሳኔዎችን ከአፍሪካ አጀንዳ 2063 ግብ ጋር አቆራኝቶ መተግበር ያስፈልጋል ብለዋል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ጤናን እንደ ስትራቴጂካዊ ብሔራዊ ኢንቨስትመንት እንደምትመለከት ገልጸው፤ ለጤና የሚመደበው በጀት በተከታታይ እየጨመረ መምጣቱንም ተናግረዋል።
በመሠረታዊ የጤና አገልግሎት ላይ የተደረገው ኢንቨስትመንት የጤና አገልግሎቶችን ወደ ማኅበረሰቡ ተደራሽ በማድረግ ሚሊዮኖችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል።
በተጨማሪም የጤና ባለሙያዎችን ቁጥር በማሳደግ የጤና ሥርዓቱን ማጠናከሯን ጠቁመው፤ ይህም በእናቶች፣ ሕፃናት እና ልጆች የመኖር ዕድል ላይ ጉልህ መሻሻል እንዲመጣ ማድረጉን ጠቁመዋል።
በአየር ንብረት ለውጥ የሚመጡ የጤና ስጋቶችን ለመቋቋምም ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብሯን በማስፋት ሚሊዮኖችን በማሳተፍ በርካታ ችግኞችን መትከሏን ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ እየተከናወነ ያለው የልማት ተግባራት ንጹሕ፣ ጤናማና ለነዋሪዎች የተሻለ የከተማ አካባቢን በመፍጠር የሕዝቡን ጤና እና የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
ዘላቂ የጤና ሥርዓት ያለ ሰላምና መረጋጋት ሊኖር እንደማይችል ገልጸው ባለፈው እሁድ ኢትዮጵያ ከተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶች የተውጣጡ ከ4 ሺህ በላይ ተመካካሪዎች የተሳተፉበትን አካታች ብሔራዊ ምክክር በማካሄድ ትልቅ ምዕራፍ አሳልፋለች ብለዋል።
ኢትዮጵያም በብሔራዊ ኢንቨስትመንት፣ በቀጣናዊ ትብብርና ለአህጉራዊ ተቋማት በማይናወጥ ድጋፍ የራሷን ድርሻ ለመወጣት ሙሉ ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።