ቀጥታ፡

የመውሊድ በዓል እሴቶችን የሕይወታችን መርህ አድርገናል - በጂንካ ከተማ የበዓሉ ታዳሚዎች

ጂንካ፤ ነሐሴ 19/2018 (ኢዜአ)--የነብዩ ሙሐመድ የልደት በዓል (መውሊድ) የበጎ አርአያነት ምሳሌ በመሆኑ የበዓሉን አሴቶች የሕይወታችን መርህ አድርገናል ሲሉ በጂንካ ከተማ የበዓሉ ታዳሚዎች ገለጹ።

1ሺህ 501ኛው የነብዩ ሙሐመድ  የልደት በዓል (መውሊድ) በጂንካ ከተማ ተከብሯል።

በክብረ በዓሉ የታደሙት የጂንካ ነዋሪዎች የመውሊድ በዓል የበጎነት ምሳሌ በመሆኑ የበዓሉ አስተምህሮ የሆኑትን አብሮነት፣ ፍቅር እና አንድነት የሕይወታቸው መርህ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ 

ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል አቶ ዳውድ ሙሐመድ የመውሊድ በዓል የበጎ አርአያነት ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዓሉ የነብዩ ሙሐመድን የፍቅርና የርህራሔ አስተምህሮ ለትውልዱ የምናስተምርበት ነው ብለዋል።

በዓሉ ሲከበር ፍቅር፣ ርህራሔ፣ ለጋስነት እና አብሮነት ጎልቶ የሚወጣበት በመሆኑ አርአያናቱ የላቀ መሆኑን ተናግረዋል።

ሌላኛዋ የበዓሉ ታዳሚ ሳውዳ አብዲ በበኩሏ የመውሊድ በዓል በጎነት የሚጎላበት የእዝነት በዓል ነው ብላለች።

ለትውልዱ በጎ ምግባርን በማስተማር፣ የተራበን በማብላት፣ የተጠማን በማጠጣት፣ የታረዘን በማልበስ እና ስለ ሀገር ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት በጋራ በመፀለይ በዓሉን ማክበራቸውንም ተናግራለች።

​የመውሊድ በዓል ከሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቱ ባሻገር ማኅበራዊ ትስስርና እርስ በርስ የመደጋገፍ እሴትን ስለሚያጠናክር ባህላዊ እሴቶቹን የህይወቷ መርህ ማድረጓን ተናግራለች።

በዓሉ የህብረተሰቡን አብሮነት የሚያጠናክሩ የተለያዩ ሰብአዊ ተግባራት የሚከናወኑበት መሆኑ ያነሱት ደግሞ ሌላው የበዓሉ ታዳሚ ሸረፈዲን አብራር ናቸው።

የነብዩ መሐመድ የልደት በዓል ያሉትን የአንድነት፣ የፍቅርና የለጋስነት አስተምህሮ በመከተል በዓሉን በአብሮነትና በመተሳሳብ እያከበሩት መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዚህም በአካባቢያቸው አቅመ ደካሞችን በማገዝ፣ ዘመድ አዝማድን በመጠየቅ፣ እንግዶችን በማስተናገድና መልካም ምኞትን በመለዋወጥ በማክበር ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

1ሺህ 501ኛው የነብዩ ሙሐመድ የልደት በዓል በጂንካ ከተማ የተከበረው በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥርአቶችና ማዕድ ማጋራት መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም