ቀጥታ፡

የመውሊድ በዓልን ስናከብር የነብዩ ሙሀመድን  አስተምህሮን በመተግበር መሆን አለበት

ጎንደር ፤ነሀሴ 19/2018 (ኢዜአ)፦ የመውሊድ በዓልን ስናከብር የነብዩ ሙሀመድን አስተምህሮ በመተግበር መሆን እንዳለበት በጎንደር ከተማ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ስብሳቢ ሼህ ኢብራሒም ሙሐመድ ገለጹ።

በጎንደር ከተማ የመውሊድ በዓል በጀሚ አልከቢር መስጂድ በድምቀት ተከብሯል። 
 

የምክር ቤቱ ዋና ሰብሳቢ ሸህ ኢብራሒም ሙሐመድ በበዓሉ ላይ እንደገለጹት የነቢዩ ሙሐመድ መወለድ በአስተምህሯቸው አማካኝነት  ለሰው ልጆች ፍቅር፣ ሠላምና እኩልነት መስፈን ትልቅ አጋጣሚ ፈጥሯል።

በአሉ ሲከበር ሀይማኖታዊ አስተምህሮውን በመተግበር  ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል ።

በአሉን በመረዳዳትና በጋራ ማክበር እንደሚገባም አስገንዝበዋል ።

ወጣቱም የበአሉን የፍቅርና የመከባበር እሴት በመረከብ ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ እንዳለበት አሳስበዋል።

የበዓሉ ታዳሚ አቶ አስረስ ሙሐመድ በበኩላቸው የመውሊድ በዓል በህዝበ ሙስሊሙ ዘንድ በደስታ የሚጠበቅና የሚከበር ነው ብለዋል።  

​በዓሉን ሃይማኖታዊ አስተምህሮው በሚያዘው መሰረት ምስኪኖችንና አቅም የሌላቸውን ወገኖች በመደገፍ እያከበርን ነው ብለዋል። 

በዓሉን በጸሎትና በሌሎች ሃይማኖታዊ ስርዓቶች እያከበሩ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሼህ ሙሀመድ አህመድ ናቸው።

በአሉን በጋራ በመሆን በፍቅርና በመተሳሰብ እያከበሩ መሆናቸውን ጨምረው ገልጸዋል ።

​በጎንደር ከተማ የመውሊድ በአል  የሀይማኖት አባቶችና ምአመናን በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም