የመውሊድ በዓልን ፍቅርና አብሮነትን በሚያጎለብቱ ተግባራት እያከበርን ነው - በዲላ የእምነቱ ተከታዮች - ኢዜአ አማርኛ
የመውሊድ በዓልን ፍቅርና አብሮነትን በሚያጎለብቱ ተግባራት እያከበርን ነው - በዲላ የእምነቱ ተከታዮች
ዲላ፣ ነሐሴ 19/2018 (ኢዜአ) ፦ የመውሊድ በዓልን ፍቅርና አብሮነትን በሚያጎለብቱ ተግባራት እያከበሩ መሆናቸውን በዲላ ከተማ የእምነቱ ተከታዮች ገለጹ።
በዲላ ከተማ 1ሺህ 501ኛ የመውሊድ በዓልን ምክንያት በማድረግ ከ2 ሺህ ለሚልቁ ወገኖች ማዕድ የማጋራት መርሀግብር ተከናውኗል።
በከተማው የሰላም መስጅድ ኢማም ሼህ ሶፍያን ጀማል ለኢዜአ እንደገለጹት በዓሉ በህዝበ ሙስሊም ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ሲሆን በዓሉንም ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ጠብቀው በፍቅርና በንድነት እያከበሩት ይገኛሉ።
በዓሉ ያሉትን የአብሮነትና የመረዳዳት እሴቶች በሚያጎለበት መልኩ ለማክበርም ከ2ሺህ ለሚልቁ ወገኖች ማዕድ የማጋራት ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።
የመውሊድን በዓል ስናከብር የነብዩ መሐመድን በጎ አርአያነት በመከተል የተቸገሩትን በመርዳትና በአብሮነት ሊሆን ይገባል ያሉት ደግሞ በከተማው የቢላል መስጅድ ኢማም ሼህ ሰይድ መሐመድ ናቸው።
በዓሉን ሐይማኖታዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ በሃይማኖታዊ ትምህርት፣ በመረዳዳት፣ በፍቅርና በአንድነት እያከበሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ከእምነቱ ተከታዮች መካከል ኡስታዝ አሊ ነጋሽ በበኩላቸው የመውሊድን በዓል በሃይማኖታዊ አስተምህሮ በሚፈቅደው መሰረት በበጎ ሥራ እያከበሩት መሆናቸውን ተናግረዋል።
በመውሊድ በዓል እርስ በርስ ያለንን አንድነት፣ ፍቅርና መደጋገፍ በማጠናከር የነብዩ መሀመድን አርአያነት በተግባር ማሳየት አለብን ሲሉም አክለዋል።