ለተማሪዎች የተደረገው ድጋፍ የተሻለ ውጤት አስገኝቷል - ኢዜአ አማርኛ
ለተማሪዎች የተደረገው ድጋፍ የተሻለ ውጤት አስገኝቷል
አዳማ፤ ነሐሴ 19/2018 (ኢዜአ)፦ ተማሪዎች ሙሉ ጊዜያቸውን በትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያውሉ በመደረጉ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ መቻላቸውን የኦልማ የአዳማ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት እና የዶዶላ ኢፋ ቦሩ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህራን ገለጹ።
በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች በሀገር አቀፍና በክልል ደረጃ የላቀ ውጤት የሚያስመዘግቡ ተማሪዎችን ለማፍራት ታስበው የተቋቋሙ ናቸው።
በኦሮሚያ ልማት ማህበር (ኦልማ) የአዳማ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ አበበ ዘውዴ ለኢዜአ እንደገለፁት በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከፍተኛ ውጤት በትምህርት ቤቱ ተመዝግቧል።
የመማር ማስተማር ዕቅዱን የጋራ በማድረግና መምህራን ከመደበኛ ማስተማር ባለፈ ለተማሪዎች እንደ በርካታ ድጋፎችን እንዲሰጡ በመደረጉ፣ ተማሪዎች ትኩረታቸውን በትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያደርጉ ማስቻሉን ገልጸዋል።
በተለይም በሀገር አቀፍ ፈተና ዝግጅት ወቅት ከተከታታይ የጥናት መርሃ-ግብር እስከ ሞዴልና ማጠቃለያ ፈተናዎች ድረስ በማዘጋጀት ለፈተናው ብቁ የሚያደርጋቸውን ልምድ እንዲቀስሙ መደረጉን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የመማር ማስተማር ሂደቱን ተማሪ ተኮር በማድረግ በንድፈ-ሀሳብ የተማሩትን በቤተ-ሙከራ በተግባር አረጋግጠው ሪፖርት እንዲያቀርቡ በመደረጉ ለፈተናው በበቂ ሁኔታ እንዲዘጋጁ መደረጉን ገልጸዋል።
በዚህም በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከፍተኛውን ውጤት በማስመዝገብ ቀዳሚ መሆን መቻላቸውን ገልጸዋል።
የዶዶላ ኢፋ ቦሩ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ዴቱ ዲቦ በበኩላቸው፤ ለስኬት ዋናው ምስጢር ተማሪዎችን ለሀገር አቀፍ ፈተናው በተገቢው መንገድ ማዘጋጀት መቻላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ተማሪዎች ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀም በቤተ-ሙከራዎች፣ በአይሲቲ ክፍሎችና በቤተ-መጻሕፍት በአግባቡ እንዲገለገሉና እንዲያጠኑ በመደረጉ የተገኘ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፈው ዓመት በትምህርት ቤቱ በሀገር ደረጃ ቀዳሚ ውጤት መመዝገቡን ያነሱት ርዕሰ መምህሩ፣ ሀገርና ትውልድን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት በትምህርት ጥራት ላይ በትኩረት እየሰሩ ለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል።
በዚህም በትምህርት ቤቱ ለሁለተኛ ጊዜ በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በተማሪ ሳዳም አብዱልአዚዝ በማህበራዊ ሳይንስ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡን አክለው ገልጸዋል።
በኦልማ የአዳማ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት 591 ነጥብ 6 ያመጣው ተማሪ ጃለል ግርማ እንዳለው፣ ሙሉ ጊዜውን በትምህርትና በጥናት ላይ በማዋሉ ይህንን ከፍተኛ ውጤት ማምጣት ችሏል።
የስኬቱ ሚስጥርም ጠንክሮ መስራትና ሙሉ ጊዜን ለጥናት መስጠት መሆኑን ተናግሯል።
በዶዶላ ኢፋ ቦሩ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበው ተማሪ ሳዳም አብዱልአዚዝ በበኩሉ፤ በምዕራብ ሐረርጌ ጭሮ ከተማ የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ተወዳድሮ ወደ ዶዶላ ኢፋ ቦሩ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት መግባቱን ገልጿል።
"የስኬቴ ሚስጥር ጠንክሮ መስራትና ማጥናት ነው" ያለው ተማሪ ሳዳም፣ ይህንን ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ የቻለው ሙሉ ጊዜውን በጥናት ላይ በማሳለፉና በዕቅድ በመመራቱ መሆኑን ገልጸዋል።
"ውጤት የሚገኘው በለፉበት ልክ ነው" ያለው ተማሪ ሳዳም፣ በርትቶ በማጠናቱ 576 ነጥብ 25 የሆነ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ተናግሯል።