ቀጥታ፡

የአፍሪካን የጤና ሥርዓት በራስ አቅም ለማዘመን የአባል ሀገራትን ትብብር ማጠናከር አስፈላጊ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 19/2018 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካን የጤና ሥርዓት በራስ አቅም ለማዘመን ኢንቨስትመንትንና የአባል ሀገራትን ትብብር ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን  የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር መሐመድ ያኩብ ጃናቢ ገለጹ።

76ኛው የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ኮሚቴ ጉባኤ በአዲስ አበባ ዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ይገኛል።

የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር መሀመድ ያኩብ ጃናቢ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ 76ኛ የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ኮሚቴ ጉባኤ በአንድ መድረክ ከመወያየት በላይ ነው።

መድረኩ የአፍሪካ የጤና ችግሮች ላይ የጋራ ውይይት በማድረግ የጋራ የመፍትሔ ሀሳብ የሚፈልቅበት መሆኑን ገልጸዋል።

በአፍሪካ በመሪዎች ቁርጠኝነት፣ በጤና ተቋማትና ባለሙያዎች ዝግጅት እንዲሁም በማህበረሰቡ ትብብር በጤና ስርዓቱ ላይ መሻሻል ታይቷል ብለዋል።

አፍሪካ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን በላይ ህዝብ ምድር መሆኗን በማንሳትም፤ አፍሪካ የጤና ስርዓቷን በራሷ አቅም ለመገንባት ጠንካራና ቀጣይነት ያለው የጤና ተቋማትን መገንባት ይገባታል ነው ያሉት።

በአፍሪካ ለተመዘገበው የጤና አገልግሎት መሻሻል የዓለም ጤና ድርጅት ያልተቋረጠ ድጋፍ ማድረጉን በመግለፅ፤ የአፍሪካ የጤና ኢንቨስትመንትን በራስ አቅም መፍጠር አስፈላጊ ነው። 

የአፍሪካ ራዕይ ግልጽ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የጤና ልህቀት ማዕከል መገንባትና የጤና ስርዓቷን በራሷ አቅም መገንባት መሆኑን በመግለጽ።

አህጉሪቱ የዕወቀትና የተፈጥሮ ሀብት ችግር የለባትም፤ መሰረታዊው ጉዳይ ተደራሽነትን ማስፋት የሚያስችል የጤና አገልግሎት መስጠት ነው ሲሉም ገልጸዋል።

የጤና ሥርዓት ዝማኔ አመራር፣ ኢንቨስትመንትና ትብብር እንደሚጠይቅ ጠቁመውም፤ የዓለም ጤና ድርጅት አፍሪካ አቅሟን እንድትገነባ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም