ኢትዮጵያ በዲጂታል ጤና ሥርዓት በሽታን በመከላከልና አክሞ በማዳን ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበች ነው - ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በዲጂታል ጤና ሥርዓት በሽታን በመከላከልና አክሞ በማዳን ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበች ነው - ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 19/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በዲጂታል ጤና ሥርዓት በሽታን በመከላከልና አክሞ በማዳን ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበች መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።
76ኛው የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ኮሚቴ ጉባኤ በአዲስ አበባ ዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄድ ጀምሯል።
በመርሃ ግብሩ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ፣ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሀሙድ አሊ ዩሱፍ፣ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፣ሀገራት የጤና ሚኒስትሮች፣ የቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ የጤና ተቋማት መሪዎች ተገኝተዋል።
76ኛው የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ኮሚቴ ጉባኤ የቀጣናውን የጤና አጀንዳ በመቅረፅ፣ ትብብርን በማጠናከር እና በአሕጉሪቱ ጤናማ፣ ደህንነቱ የተጠበቀና ፈተናዎችን የሚቋቋም ማህበረሰብ መገንባት ያስችላል።
ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ መድረኩን ማዘጋጀቷ በቀጣናው በትብብር ላይ የተመሰረተ የጤና ስርዓት ለመፍጠር ያላትን ጠንካራ ቁርጠኝነት ያሳያል።
ኢትዮጵያ ከዓለም ጤና ድርጅትና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር የጤና ስርዓቷን በማጠናከር እና ሀገራዊ ትኩረት የሚሰጣቸው የጤና ጉዳዮችን በማሳካት በኩል ያስመዘገበችውን መሻሻል ለማሳየት ዕድል ይፈጥራል።
በኢትዮጵያ መሰረታዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ማስፋት፣ የጤና ስርዓት አፈፃፀምን ማጠናከር እና የማርበርግ ቫይረስ በሽታ ወረርሽኝን በተሳካ ሁኔታ መቆጣጠርን ጨምሮ የተመዘገቡ ስኬቶች አይበገሬ የጤና ስርዓት ለመገንባት ያላትን ዘላቂ ጥረት የሚያሳይ ነው።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች በጤና ስርዓቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደሩ ነው።
ኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትንና ጥራትን በዘላቂነት ለማሻሻል ብሔራዊ የጤና ስትራቴጂ ቀርፃ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የህክምና ባለሙያዎችን በማብቃትና የህክምና መገልገያዎችን በማዘመን የእናቶችና ህፃናትን ሞት በመሰረታዊነት መቀነስ ተችሏል ብለዋል።
የዲጂታል የጤና ስርዓትን በማሳደግ የጤና እና የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት የማቹሪቲ ሌቭል 3 መድረሷን ገልጸው፤ የሀገር ውስጥ ምርት ከኢንዱስትሪ ፖሊሲ ያለፈ የጤና ስትራቴጂ ነው ብለዋል።
ቴክኖሎጂ በዜጎች የጤና ሥርዓት ላይ መሰረታዊ ለውጥ እያመጣ መሆኑን በማንሳት፤ ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ብዙ ልምድ መገኘቱን ተናግረዋል።
አፍሪካ የዕውቀትና የክህሎት ችግር የለባትም፣ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት አሟጦ መጠቀም ይገባል ብለዋል።
ለአፍሪካ የጤና ሉዓላዊነት የሀገር ውስጥ ምርት ወሳኝ መሆኑን በማንሳት፣ ኢትዮጵያ ከአፍሪካውያን ጋር በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።