ቀጥታ፡

የጤና ሥርዓትን በዲጂታል ቴክኖሎጂና በሰው ሰራሽ አስተውሎት ማጠናከር ለአፍሪካ የወደፊት የጤና ሉዓላዊነት ቁልፍ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 19/2018 (ኢዜአ)፦ የጤና ሥርዓትን በዲጂታል ቴክኖሎጂና በሰው ሰራሽ አስተውሎት ማጠናከር ለአፍሪካ የወደፊት የጤና ሉዓላዊነት ቁልፍ መሆኑን በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) የሥራ አስፈፃሚ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቦባክሪ ዲያው ገለጹ።

76ኛው የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣናዊ ኮሚቴ ጉባኤ በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ነው።

በመርሀግብሩ የኢፌዴሪ ፕሬዝደንት ታዬ አጽቀስላሴ፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሀሙድ አሊ ዩሱፍ፣ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፣ የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር መሀመድ ያኩብ ጃናቢ ተገኝተዋል።

በተጨማሪም ከ47ቱ የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ አባል ሀገራት የተውጣጡ የጤና ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ የጤና ባለሙያዎች፣ የልማት አጋሮች እንዲሁም የቀጣናውና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች መሪዎች ታድመዋል።

ጉባኤው በጤና ዘርፍ በአምስት ምሰሶዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ይካሄዳል።

እነኚህም በአፍሪካ ዘላቂ የጤና ፋይናንስ ስርዓት መገንባት፣ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤ፣ ዲጂታል የጤና ስርዓት መገንባት፣ የጤና ባለሙያዎች አቅም ግንባታና የሀገር ውስጥ ምርቶችን ማሳደግ ናቸው።

በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) የሥራ አስፈፃሚ ጽሕፈት ቤት ሀላፊ አቦባክሪ ዲያው በዚሁ ወቅት እንዳሉት የውጭ የጤና ድጋፍ መቀነስ፣ ደካማ የፋይናንስ አቅም እና የትግበራ ክፍተት በቀጣናው የጤና ስርዓት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ጠቅሰዋል።

የጤና ሉዓላዊነት ማለት አፍሪካ የራሷን የጤና ቅድሚያዎች በራሷ የመወሰን፣ የጤና ሥርዓቶቿን የመደጎም፣ መረጃዎቿን የማስተዳደር፣ አስፈላጊ የጤና ምርቶችን በራሷ የማምረት እና ወደፊት ሊያጋጥሙ ከሚችሉ ቀውሶች ሕዝቦቿን የመጠበቅ አቅም ማለት ነው ብለዋል።

ጤናን ከመደበኛ ማኅበራዊ ወጪ ወደ ምርታማ ኢኮኖሚያዊ ኢንቨስትመንት መቀየር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የተበታተነ አሠራርን ወደ አንድ ተአማኒ የአሰራር ሁኔታ ማምጣት እንደሚገባ ነው ያመላከቱት።

ኢትዮጵያ በዲጂታል መለያ፣ የጤና መረጃ ሥርዓቶች ተናባቢነት፣ የወጪ አፈጻጸምን መከታተልና በመረጃ የተደገፈና በሰው ሠራሽ አስተውሎት የታገዘ ውሳኔ አሰጣጥ በአንድ ላይ ማጠናከር እንደሚቻል ማሳያ መሆኗን ጠቅሰዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት እና የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የሚያከናውኗቸው ሥራዎች እጅግ ተደጋጋፊ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የጤና ሥርዓትን በዲጂታል ቴክኖሎጂና በሰው ሰራሽ አስተውሎት ማጠናከር ለአፍሪካ የወደፊት የጤና ሉዓላዊነት ቁልፍ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም