ቀጥታ፡

የመውሊድ በዓል በአብሮነት እና እርስ በርስ በመረዳዳት እያከበርን ነው - የእምነቱ ተከታዮች

ሐረር፤ ነሐሴ 19/2018 (ኢዜአ)፦ የመውሊድ በዓል በፍቅር፣ በአብሮነት እና እርስ በርስ በመረዳዳት እያከበሩ መሆኑን በሐረር የእምነቱ ተከታዮች ገለጹ።

1 ሺህ 501ኛው የመውሊድ በዓል በሐረር ከተማ የሃይማኖት አባቶች፣ የእምነቱ ተከታዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ከማለዳው ጀምሮ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስነ-ስርዓቶች በመከበር ላይ ይገኛል።

የበዓሉ ታዳሚዎች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የመውሊድ በዓልን በፍቅር፣ በአብሮነት፣ እርስ በርስ በመጠያየቅና በመረዳዳት በደመቀ ሁኔታ እያከበሩት ይገኛሉ።

ከበዓሉ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ሳላህ ዩሱፍ፤ "የመውሊድ በዓል በሰዎች መካከል ፍቅርን፣ አብሮነትን፣ አንድነትንና የመረዳዳት ባህልን የሚያጠናክር ነው" ሲሉ ገልጸዋል።

አክለውም በዓሉን ሃይማኖታዊ ስርዓቱ በሚያዘው መሰረት በድምቀት እያከበሩት እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ሌላው የበዓሉ ተሳታፊ ወጣት ዚያድ አርጋው በበኩሉ፤ የመውሊድ በዓልን ከሌሎች ወንድምና እህቶቹ ጋር አብሮነትን በማጠናከር በሰላምና በደስታ እያሳለፈ እንደሚገኝ ተናግሯል።

አክለውም በዓሉን የነቢዩ መሀመድን አስተምህሮ በመከተል የተቸገሩትን በመርዳትና በመደገፍ እያከበረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ወጣት ያስሚን ሙክታር በበኩሏ፤ የነቢዩ መሐመድ መውሊድን በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስነ-ስርዓቶች ከማክበር ባሻገር በጎ ሥራዎችን በማከናወንና ያላቸውን ለሌሎች በማካፈል ማከበር እንደሚገባ ተናግራለች።

የመውሊድ በዓልን ሃይማኖታዊ አስተምህሮውን በጠበቀ መልኩ በድምቀት እያከበሩ እንደሚገኙ ሌላው የበዓሉ ተሳታፊ ኢማድ ሳለሃዲን ገልጸዋል።

አክለውም በዓሉን ያላቸውን በማካፈል፣ በመረዳዳትና አንድነትን በማጠናከር የነብዩ መሐመድን መልካም ተግባራት በማስታወስ እያከበሩት እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም