ቀጥታ፡

አፍሪካውያን በዓለም የጤና ስርዓት ሪፎርም ላይ በንቃት በመሳተፍ የጋራ አቋም መያዝ አለባቸው - የዓለም ጤና ድርጅት

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 19/2018 (ኢዜአ)፦ አፍሪካውያን በዓለም የጤና ስርዓት ሪፎርም ላይ በንቃት በመሳተፍ የጋራ አቋም መያዝ እንዳለባቸው የዓለም ጤና ድርጅት ገለጸ።

76ኛው የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ኮሚቴ ስብሰባ በአዲስ አበባ ዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄድ ጀምሯል።

በመርሃ ግብሩ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ፣ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሀሙድ አሊ ዩሱፍ፣ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፣ የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር መሀመድ ያኩብ ጃናቢ፣ የአፍሪካ ሀገራት የጤና ሚኒስትሮች፣ የቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ የጤና ተቋማት መሪዎች ተገኝተዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ስብሰባውን በተመለከተ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት፤ አፍሪካ የሚከሰቱ ወረርሽኞችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚወስዱት እርምጃ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ነው።

የአፍሪካ በሽታን የመከላከልና የመቆጣጠር አቅም እያደገ መምጣቱን ገልጸው፤ ሀገራት ትብብራቸውን ማጠናከር አለባቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የማርበርግ ወረርሽኝን በ90 ቀናት ብቻ መቆጣጠርና ማጥፋት መቻሏ የአፍሪካውያን የማድረግ አቅም እያደገ ለመምጣቱ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

በአፍሪካ ዕምቅ ዕውቀትና የተፈጥሮ ሀብት እንዳለ በማንሳት፣ የሀገር ውስጥ የመድሀኒትና የህክምና መገልገያ ግብዓቶችን ምርት ማሳደግ ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የዓለም ጤና ድርጅት የማቹሪቲ ሌቭል 3 መድረሳቸውንም ዋና ዳይሬክተሩ ጨምረው አስታውቀዋል።

አፍሪካውያን ትብብራቸውን በማጠናከር ከውጭ ጣልቃ ገብነት ነፃ ሆነው የሀገር ውስጥ ምርታቸውን ማሳደግ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

በቀጣይም የአፍሪካን የጤና ስርዓት በአፍሪካ አቅም ለመገንባት ቀጣይነት ያለው የፋይናንስ ምንጭ መፍጠር አለባቸው ብለዋል።

በዓለም የጤና ስርዓት ሪፎርም ላይ ንቁ ተሳታፊ መሆን የሚያስችላቸውን ትብብርና ቅንጅት መፍጠር ይገባቸዋል ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም