በዓሉን በጋራ እና አቅመ ደካሞችን በመደገፍ እያከበርን ነው - የሃይማኖት አባቶችና ምዕመናን - ኢዜአ አማርኛ
በዓሉን በጋራ እና አቅመ ደካሞችን በመደገፍ እያከበርን ነው - የሃይማኖት አባቶችና ምዕመናን
ጅማ፤ ነሐሴ 19/2018 (ኢዜአ)፦ የመውሊድ በዓልን በጋራ እና አቅመ ደካሞችን በመደገፍ እያከበርን ነው ሲሉ የጅማ ከተማ የሃይማኖት አባቶችና የእምነቱ ተከታዮች ገለጹ።
1 ሺህ 501ኛው የመውሊድ በዓል በጅማ ከተማና አካባቢው በደማቅ ሁኔታ እየተከበረ ይገኛል።
በዓሉ በተለይም በጅማ መድረሰቱል ከይርያ ቅጥር ግቢ ውስጥ በመተሳሰብ፣ በመረዳዳትና አቅመ ደካሞችን በመመገብ እየተከበረ ነው።
የጅማ ታላቁ ሙኒር መስጂድ ኢማም ሼህ መሐመድ አባዲጋ፣ መውሊድን ስናከብር የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብና በመረዳዳት በጋራ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
መውሊድ የደስታና የሰላም በዓል መሆኑን የጠቀሱት ሼህ መሐመድ፤ የተቸገረን በመጠየቅ፣ የተራበን በመመገብ፣ የተራቆተን በማልበስ እና ለሌሎች ደስታ በመሆን ልናስበው ይገባል ብለዋል።
ይህንን በዓል ምክንያት በማድረግም ከአምስት ሺህ በላይ አቅመ ደካሞችን መመገብ መቻሉን ተናግረዋል።
ሌላው የእምነቱ ተከታይ አባስ አብዱሰላም በበኩሉ፣ የመውሊድ በዓል ትርጉሙ የሚሟላው የተቸገሩትን ስናስብና ለሌሎች ደስታ ስንሆን ነው ብሏል።
ከትናንት ጀምሮ ከጎሮቤትና በአካባቢው የሚገኙ አቅመ ደካሞችን በመርዳት እያሳለፈ መሆኑን የገለጸው አባስ፣ ይህንን በጎ ተግባር ወደፊትም እንደሚቀጥል ተናግሯል።
በበዓል ወቅት ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ጊዜ መደጋገፍና በጋራ መኖር እንደሚያስፈልግ የገለጹት ደግሞ አሚር ጠሃ እና በሀቁ ኑሩ ናቸው።
በተለይም በመውሊድ በዓል ወቅት ይህንን የመረዳዳትና የመተሳሰብ ባህል ማጠናከር እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በጅማ ከተማ የሚከበረው የመውሊድ በዓል ሃይማኖታዊ እሴቱን በመጠበቅ በመተሳሰብና በመረዳዳት በጋራ እየተከበረ መሆኑ ተገልጿል።