ቀጥታ፡

የመገጭ ግድብ ግንባታ ወደ ማጠናቀቂያ ምዕራፍ ደርሷል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 19/2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ አቅራቢያ እየተገነባ የሚገኘው የመገጭ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ ወደ ማጠናቀቂያ ምዕራፍ መድረሱን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ የመገጭ የግድብ ግንባታ ያለበትን ደረጃ ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ለተውጣጡ ጋዜጠኞች አስጎብኝቷል።

ሚኒስቴሩ የኢትዮጵያን በምግብ ራስን የመቻል ጉዞ የሚያሳኩ የመስኖ ልማት መሰረተ ልማቶችን እያስፋፋ ይገኛል።

ከእነዚህ መሰረተ ልማቶች መካከል በአማራ ክልል ጎንደር አቅራቢያ እየተገነባ የሚገኘው መገጭ ግድብ አንዱ ሲሆን ግድቡ ከተጀመረ ረዘም ያለ ጊዜ አስቆጥሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ግድቡ በፍጥነት ተጠናቆ አገልግሎት እንዲሰጥ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረትም በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ግድቡን ለማጠናቀቅ በተደረገው ርብርብ አሁን ላይ ወደ ማጠናቀቂያ ምዕራፍ ደርሷል።

በመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የመስኖ ፕሮጀክቶች ፕሮግራም ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ እንጂነር አሸናፊ ሊካሳ በሰጡት ማብራሪያ ግንባታው በመጓተቱ ምክንያት ግንባታውን ይዞ የነበረው ተቋራጭ በአዲስ እንዲተካ መደረጉን አንስተዋል።

አሁን ላይም ግድቡን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ሁሉን አቀፍ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።

የውሃ መስኖ መቆጣጠሪያው ሲቪል ስራ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን ጠቁመው፤ የኤሌክትሮ መካኒካል ስራው በሂደት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ግድቡ በአሁኑ ወቅት ውሃ መያዝ መጀመሩን ጠቅሰው፤ እስካሁን 33 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ መያዙንም ተናግረዋል።

የግድቡ ግንባታ 94 በመቶ መድረሱን ጠቁመው፤ የግዱቡ የውሃ ማስተንፈሻ ስፒልዌይ ስራም መጠናቀቁን ገልጸዋል።

የግድቡ ግንባታ መሉ በሙሉ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር በርካታ ነዋሪዎችን በመስኖ ልማትና በመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም