የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኤአይ፣ የዲጂታል ጤና እና የአረንጓዴ ልማት ራዕይ የሚደነቅ ነው -በኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ - ኢዜአ አማርኛ
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኤአይ፣ የዲጂታል ጤና እና የአረንጓዴ ልማት ራዕይ የሚደነቅ ነው -በኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18/2018 (ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰው ሠራሽ አስተውሎትን (AI) እና የዲጂታል ጤና ቴክኖሎጂዎችን ከሀገራዊ የልማት እንቅስቃሴዎች ጋር በማቀናጀት እያከናወኑ ያሉትን አርቆ አሳቢነትን የተከተሉ ስራዎች የሚደነቁ መሆናቸውን በዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ፍራንሲስ ቺሳካ ካሶሎ ገለጹ።
ሀገራዊ የልማት እንቅስቃሴዎቹ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን፣የከተሞች ማዘመን እና የወንዞች ዳርቻ ልማት ስራዎችን ያካተቱ ናቸው።
በኢትዮጵያ፣በአፍሪካ ህብረት እና በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (UNECA) የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ፍራንሲስ ቺሳካ ካሶሎ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ የማህበረሰብ ጤና ተደራሽነትን በማስፋት ሂደት ውስጥ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ረገድ ግንባር ቀደም ሀገር ናት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአፍሪካ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) እና የዲጂታል ጤና አምባሳደር ናቸው፤ በዚህም ከአፍሪካ ህብረት እውቅና እና ሽልማት አግኝተዋል ብለዋል።
ተወካዩ አክለውም በጤናው ዘርፍ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ለማስፋፋት በሚደረገው ጥረት የዓለም ጤና ድርጅት ከኢትዮጵያ መንግስት እና ከጤና ሚኒስቴር ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
የአየር ጥራትን ማሻሻል እና ደህንነቱ የተጠበቀ አካባቢን መፍጠር የመተንፈሻ አካላት በሽታዎችን እና የካንሰር ስጋቶችን እንደሚቀንስ በመግለጽ፣ የአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲዎች ለህዝብ ጤና ወሳኝ ምሰሶ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ከዚህ አኳያም የኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እና የከተማ ልማት ተግባራት ከጤና ጥበቃ እና ቅድመ-መከላከል ስራዎች ጋር የተሳሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አረንጓዴ አሻራ የአየር ጥራትን ያሻሽላል፤ ንጹህ አየር ደግሞ ለተሻለ ጤንነትና የመተንፈሻ አካላት በሽታዎችን ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል ሲሉ አስረድተዋል።
የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት የአካባቢ ጽዳትና ንፅህናን በማስጠበቅ ረገድ ያለውን የጤና ጥቅም በአጽንኦት አንስተዋል።
የኮሪደር ልማቱ የአካባቢ ጽዳትን እንደሚያሻሽል የጠቆሙት ተወካዩ፣ ስራው በሀገር አቀፍ ደረጃ መስፋቱ በውሃ ወለድ አምጪ ተህዋሲያን የሚመጡ በሽታዎችን እንደሚቀንስ አመልክተዋል።
መንግስት የከተሞችን ውበት ከማስጠበቅ ባለፈ የአየር ጥራትንና የህዝብን ጤና ለመጠበቅ በአረንጓዴ መሰረተ ልማቶች ላይ እያፈሰሰ ያለው ሀብትና የሰጠው ትኩረት ሊደነቅ የሚገባው ነው ብለዋል።
በአረንጓዴ መሰረተ ልማት እና ጤናማ ከተሞች (healthy cities) እንዲሰፉ የሚያፈሰው መዋዕለ ንዋይ ከተሞችን ከማስዋብ ባሻገር፣ የህዝብን ጤና በዘላቂነት ለመጠበቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ነው የገለጹት።
በዚህ ረገድም መንግስት ትኩረቱን ከህክምና ወጪ ይልቅ በሽታን ወደ መከላከል አቅጣጫ በማዞር በቅድመ-መከላከል ስራዎች ላይ እያከናወነ ያለውን ስራ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተናግረዋል።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ተሞክሮ በመላው አፍሪካ ሊደገም እንደሚገባ ተወካዩ አስገንዝበዋል።