የደባርቅን የመልማት ፀጋ ወደ ተጨባጭ አቅም ለመቀየር ከተማዋን በመሰረተ ልማት ማበልጸግ ይገባል - ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
የደባርቅን የመልማት ፀጋ ወደ ተጨባጭ አቅም ለመቀየር ከተማዋን በመሰረተ ልማት ማበልጸግ ይገባል - ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18/2018 (ኢዜአ)፦የደባርቅን የመልማት ፀጋ ወደ ተጨባጭ አቅም ለመቀየር ከተማዋን በመሰረተ ልማት ማበልጸግ እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።
የደባርቅን ከተማ ለማልማት የተዘጋጀ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር "ደባርቅን እናሳምር ከተማችንን እናድምቅ" በሚል መሪ ሀሳብ በሂልተን ሆቴል እየተካሄደ ይገኛል።
በመርሃ ግብሩ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና ባለሀብቶች ተገኝተዋል።
በገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩ "ኑ ተፈጥሮ የገለጠችውን ድንቅ የቱሪስት መስህብ የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ መግቢያ በር የሆነችውን ደባርቅ ከተማ በጋራ እናልማ" የሚል ጥሪ ቀርቧል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ደባርቅ የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ መግቢያ ከተማ ናት።
ይሁን እንጂ ደባርቅ የታሪክ ባለቤትነቷን፣ የቱሪዝም መተላለፊያነቷን የሚመጥን ልማት አልታደለችም ብለዋል።
የደባርቅን የመልማት ፀጋ ወደ ተጨባጭ አቅም መለወጥ የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመሩንም ጨምረው ገልጸዋል።
በመሆኑም ከተማዋን በማልማት የተፈጥሮ ውበቷን ለመግለጥ ሁሉም በጋራ ትብብር ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።
የደባርቅ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ከንቲባ ጌትነት ፀጋየ በበኩላቸው፤ ደባርቅ የቀድሞ የሰሜን አውራጃ ከተማ፣ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ መገኛ የቱሪዝም ቀዬ መሆኗን ገልጸዋል።
ደባርቅ በተፈጥሮ ሀብቶች የበለጸገች የቱሪዝም ማዕከል ብትሆንም የሚገባትን ያህል መልማት ባለመቻሏ የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ ማራዘም አልቻለችም ነው ያሉት።
ስለሆነም መንግሥት ያመጣው የኮሪደር ልማት ተቋዳሽ እንድትሆን ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።